Sunday, 30 December 2012

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቁጣቸውን እየገለጹ ነው


በሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ ከአገር መባረር ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ቁጣቸውን እየገለጹ ነውሐራ ዘተዋሕዶ

December 29, 2012

  • ሊቀ ካህናት ለጉባኤው መግለጫ ይቅርታ እንዲጠይቁ ለሰዓታት ጫና ተደርጎባቸዋል
  • ‹‹አጀንዳዬ ሃይማኖታዊ ነው፤ የሠራኹት ስሕተት ይኹን የምጠይቀው ይቅርታ የለም !!››
  • የሰላምና አንድነት ጉባኤው መግለጫ እንደሚያወጣ ይጠበቃል
  • መንግሥት በወሰደው ርምጃ የመንበረ ፕትርክና ዓላሚዎቹ ጳጳሳት እጅ እንዳለበት ታምኖበታል


Letest Ethiopian Orthodox Tewahido Churchሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ ከብፁዓን አበው ጋር  በተወሰኑ ጳጳሳት ግፊትና በመንግሥት የደኅንነት ኀይሎች ርምጃ ትላንት ምሽት ከኢትዮጵያ ተገደው እንዲወጡ የተደረጉት ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ ከጥቂት ሰዓታት በፊት አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ደርሰዋል፤ በሰላምና አንድነት ጉባኤው አባልም አቀባበል እንደተደረገላቸው ታውቋል፡፡ በሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ላይ ስለተፈጸመው ተግባር መረጃው የደረሳቸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአሁኑ ወቅት በጉዳዩ ላይ እየመከሩበት ሲኾን ርምጃውን አነሣስተዋል፤ ግፊት አሳድረዋል በተባሉ ግለሰቦችና ጳጳሳት ላይ ጠንካራ አቋም ይወስዳሉ ተብሎ ይጠበቃል፤ ጳጳሳቱን ያሳተፈውና ለመንግሥት ጣልቃ ገብነት ማረጋገጫ ተደርጎ የተወሰደው ይኸው ርምጃ የማክሰኞውን የቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ እንዳያጋግለው ተፈርቷል፡፡

በቀዳሚው የዜና ዘገባችን እንዳስነበብነው÷ ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ትላንት ከሰዓት በኋላ ፒያሳ ከሚገኘው ቤታቸው ወደ ቦሌ ለስብሰባ ቀጠሮ ብለው ከወጡ በኋላ ነበር ታግተው ቆይተው በዚያው ‹‹ትኬት ተቆርጦላቸው›› ተገደው እንዲወጡ የተደረገው፡፡ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ዋነኛው ሰው የኾኑት ልኡኩ በግዳጅ እንዲወጡ ከመደረጋቸው በፊት እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ ባገቷቸው የደኅንነት ኀይሎች በተለያዩ ጥያቄዎችና ተጽዕኖዎች ሲዋከቡ እንደነበር ተገልጧል፡፡ ረቡዕ ዕለት አዲስ አበባ በደረሱበት ወቅትም ሊቀ ካህናትና አብረዋቸው የነበሩት ሌላው ልኡክ በልዩ ክፍል እንዲገቡ ተደርጎ ጥብቅ ፍተሻ እንደተካሄደባቸው ታውቋል፡፡

Monday, 24 December 2012

ከሶማሊያውያን የሚበልጡ ኢትዮጵያዊያን ተሰደዋል


ኦሮሞ፣ ኦጋዴን፣ አማራና ትግራይ በደረጃ ተቀምጠዋል

immigrants


የአራት ዓመት ማነጻጸሪያ የቀረበበትን የሪፖርቱ አንያንዳንዱ ክፍል ያስገርማል። የማነጻጸሪያው ማሳረጊያ አስደንጋጭ ነው። መረጃው በአሃዝ፣ በኩኔታ፣ በባህሪው ስደትን ይገልጻል። ትንታኔው በካርታ፣ በስደቱ መነሻና መድረሻ መካከል፣ እንዲሁም በስደት መዳረሻ ላይ የሚያጋጥመውን አፈና፣ ቶርቸር፣ አስገድዶ መደፈር፣ ስቃይ፣ የባህር ሲሳይ የሆኑ ወገኖችን ይጠቅሳል።
በተለይ በምስራቅ አፍሪቃ በኤርትራ፣ በኢትዮጵያ  በኬንያ፣ በጅቡቲ፣ በሶማሊያና፣ፑንት ላንድ፣ ሶማሊ ላንድ፣ ስደትና የስደትን አስከፊነት በሪፖርቱ ተዘርዝሯል። አገራችን ኢትዮጵያ በስደት የተለዩዋት ዜጎቿ ቁጥር አገር አልባ ከሆነችው ሶማሊያ የሚልቅበትን ሁኔታ ያመላክታል።
የዓለም የስደተኞች ኮሚሽን ከፍተኛ ኮሚሽርን /UNHCR/ በመጥቀስ የኖቬምበር 2012 ሪፖርቱን ያቀረበው Regional Mixed Migration Secretariat /RMMS/ የተባለው ከኢሚግሬሽን ድርጅት ጋር የሚሠራውና በአውሮጳ ኮሚሽን እና በሌሎች ድጋፍ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ከ2009 – 2012 ከኢትዮጵያ ወደ የመን የተሰደዱትን ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከሶማሊያ ጋር በማነጻጸር ያቀርባል። በዚህ ማነጻጸሪያ መሰረት 223ሺህ 770 ወገኖች ወደ የመን በነፍስ ግቢ በነፍስ ውጪ የባህር ጉዞ ወደ የመን አቅንተዋል። በተመሳሳይ ከሶማሊያ 100ሺህ 845 ሰዎች የመን በተመሳሳይ ገብተዋል። እንግዲህ እዚህ ላይ ነው አሳሳቢውና አስደንጋጩ ጉዳይ የሚነሳው።
በኢኮኖሚ ከዓለም አገሮች ሁሉ እጅግ ተመንጥቃ ባለሁለት አሃዝ እያደገች መሆኗ የሚነገርላት ኢትዮጵያ ወደ የመን ብቻ ከገቡት ስደተኞች በችግርና ያለ አስተዳዳሪ መንግሥት ሁለት አስርተ ዓመታት ካሳለፈችው ከሶማሌ በመቶ ሺህ ስምንት መቶ ይበልጣሉ።

Sunday, 16 December 2012

ሰንበት ምሳ፤ ኢትዮጵያ መድሃኒያለም እና ኤርትራ ኪዳነምህረት በኬኒያ



ይህ ፅሁፍ ለአዲሳባዋ ፍትህ/አዲስ ታይምስ ተልኮ ነበር። እነሆ ለርሶም፤ሰላም ወዳጄ እንዴት ሰነበቱልኝ… ሀገሩ ሰፈሩ ሁሉ አማን ሁሉ ሰላም ነው…? “በሰላም ውላችሁ በደህና እንድትገቡ” የሚል መዝሙር ድሮ ድሮ በየ ጠዋቱ ከራዲዮን ዜና በኋላ እንሰማ ነበር። እርሷን ሙዚቃ ጋብዤዎታለሁ፤ ልልዎ ፈልጌ ከየት አግኝተው ይሰሟታል ብዬ ትቼዋለሁ። ነገር ግን ያለ ሙዚቃ ግብዣም ቢሆን በሰላም ወጥተው በሰላም አንዲገቡ ምኞቴ ነው!ዛሬም ኬኒያ ነን። አንድ ጊዜ “ኬኒያን በደርበቡ” ካልኩዎት በኋላ ክፍል ሁለት ክፍል ሶስት እያልኩ ከማደክምዎ ይልቅ በተለያየ ርዕስ ብቅ ብል ይሻላል ብዬ ነው ይህንን ርዕስ የሰጠሁት፤ ሌላም ምክንያት አለኝ…ደሞስ እስከመቼ በድርበቡ እንላታለን! አንዳንዴም የፈጀውን ይፍጅ ብለን ገባ ብለን እናያታለን አንጂ… ደሞ ለኬኒያ!ጀመርን!ባለፈው ጊዜ በዚች አዲስ ታይምስ ላይ የወጣች ጨዋታችንን በውጪ ሀገር ለሚገኙ ወዳጆችም ትድረስ ብዬ በኢንተርኔት አስተላልፊያት ነበር። ምነው እንኳ በኬኒያ ስለ “ኬዝ” ጋገራ የምታወራው… እ…! ታድያልዎ አንዳንድ ወዳጆቻችን በፅሁፏ ላይ ተቃውሞ አሰምተዋል። የተቃውሞው መነሾ አንድም፤ “ይህንን ጨዋታ ፈረንጆቹ ቢያገኙት ወይም በስሚ ስሚ ቢሰሙት በየበረሃው በስደት የሚጉላላውን ኢትዮጵያዊ ላይ ጭራሽ ይጨክኑበታል።” የሚል ሲሆን ሌላው ደግሞ፤ “የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች… አሉ” … “ወንድ ከሆን… አንተ ራስህ ምን “ኬዝ” እንዳስጋገርክ አታወራም…? “አንተ ምንትስ አንተ ቅብርጥስ አንተ… ወዘተ…!” በሚል ልክ ልኬን (ልክ ልኬን አንኳ አይደለም አብዛኛዎቹ ጠበውኛልም አጥረውኛልም…!) ብቻ ግን ነግረውኛል!የሆነው ሆኖ ግን እንደኔ እምነት አንድ “የሚፅፍ” ግለሰብ ያየውን የሰማውን ሳይደብቅ ቢያወራ ሃላፊነቱን በአግባቡ ተወጣ ነው የሚባለው። እኔም ያደረግሁት እርሱኑ ነው። “ህይወትን ከነቡግሯ መሳል” እንዲል፤ ጋሽ ስብሐት ለአብ! ዋናው እውነት መሆኑ ነው እንጂ! ምንም ነገር ቢሆን ከመፃፍ አያመልጥም ብዬ አስባለሁ።


Friday, 14 December 2012

በመቀሌ ከተማ ጋዜጣ”መፅሄትና መፃሕፍት በማዞርና መንገድ ዳር በመዘርጋት ሽጠው የሚተዳደሩ ወገኖች ስራቸውን እንዲያቆሙ ታዘዙ


ታህሳስ ፭(አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- በመቀሌ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ወጣቶች”ህፃናትና ኣዛውንቶች ከታሕሳስ 5/2005ዓ/ም ጀምረው ስራቸውን እንዲያቆሙ የከተማው ኣስተዳደር ከፖሊስና ሚሊሻ ሓይሎች ጋር በመቀናጀት ኣስቁመዋቸዋል$ እነዚህ ወገኖች ጋዜጣ”መፅሄትና መፃሕፍት በማዞር”መንገድ ዳር ተቀምጦው በመሸጥ የዕለት ገቢያቸው ንየሚያገኙ ሲሆኑ የከተማው ኣስተዳደር ጋዜጣና መፅሄት እንዳያዞሩና ኣንድ ቦታ ላይ ተቀምጠውም እንዳይሸጡ  ያዘዘ ሲሆን፣  ያላቸው መጽሄት እና ጋዜጣ ሽጠው እንዲጨርሱ የኣምስት ቀን ዕድል ሰጧቸዋል
እነዚህ ወገኖች  “እኛ ሰርተን ራሳችንን ችለን ለመኖር ያለንን ብቸኛ ዕድል ሊነፈገን ኣይገባም$ ይህንን የምትከለክሉን ከሆነ ኣንድ ላይ ተሰባስበን የምንሸጥበት ቦታ ስጡን ወይም ሌላ የተሻለ የስራ ዕድል ስጡን” የሚል ጥያቄ ቢያቀርቡም !የከተማው ባለስልጣናት “ለናንተ የሚሆን የመሸጫ ቦታ ይሁን ሌላ የስራ ዕድል የለንም$ ከፈለጋችሁ ወደየመጣችሁበት ወረዳ ተመልሳችሁ መስራት ትችላላችሁ$ “የሚል ኣሳዛኝ መልስ እንደተሰጣቸው ገልፀዋል$
በፖሊስ”በሚሊሻና በካድሬ እየተባረረ የተገኘ ወጣት ሲናገር “እኛ ሰርተን ለፍተን ደክመን የሰው እጅ ከማየትና ማጅራት መትተን የሰው ሀብት ከመዝረፍ እንላቀቅ ብለን ስንቀሳቀስ መንግስት ሊያበረታታን ይገባል እንጂ ሊያሳድደንና እግር እግራራችን እየተከተለ ሊያባርረን ባልተገባ ነበር$ እኔ ኣሁን በእጄ ላይ ያሉት መፃሕፍቶች በውድ ዋጋ የገዛሁዋቸው  ናቸው ፣ ነገር ግን እንድንነሳ የተሰጠን ቀን ገደብ 5 ቀን ብቻ ስለሆነ የግደ ትልቅ የዋጋ ቅናሽ ኣድርጌና ከስሬ መሸጥ እገደዳሎህ$ ኣልበለዚያ ንብረቴን ዘርፈው ሊያስሩኝ  እንደሚችሉ በስብሰባው ለሁሉም ጋዜጣና መፅሄት ኣዟሪዎችና መንገድ ዳር ላይ ተቀምጠን ለምንሸጥ ተነግሮናል” ሲል በምሬት ተናግረዋል$ አንድ የተቃዋሚ አባል ” የትግራይ መስተዳዳር የወሰደው እርምጃ የትግራይ ህዝብ ህወሀት ከሚያቀርበው መረጃ ውጭ ሌላ መረጃ እንዳያገኝ ለማድረግ ነው” በማለት ተናግረዋል።

ፌዴራል ፖሊስ አገሪቱን በስለላ ካሜራዎች ለማጥለቅለቅ አቅዷል


ታህሳስ ፭(አምስት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም

ኢሳት ዜና:- የፌዴራል ፖሊስ ከሁለት ዓመት በፊት በአዲስአበባ ተክሎ ሥራ ላይ ያዋላቸው የስለላ ካሜራዎች (cctv ካሜራዎች)
ውጤታማ በመሆናቸው ወደክልሎች ለማስፋፋት ማቀዱን አስታወቀ፡፡ ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ እንዳመለከተው በኢትዮጵያ የፖሊስ ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስአበባ ዋናዋና መንገዶች ላይ ካሜራዎችን በመግጠም የመቆጣጠሪያ ክፍል በማቋቋም በመንገዶቹ ላይ የሚሰሩ ሕገወጥ ድርጊቶችንና የትራፊክ አደጋዎችን በአነስተኛ የፖሊስ ኃይል ያለብዙ ወጪና ድካም ለመቆጣጠርና ጸጥታ ለማስከበር መቻሉን ይጠቅሳል፡፡

ይህንኑ ቴክኖሎጂ በከተማውና በክልሎች ለማስፋፋትና ተጨማሪ ሥራ እንዲያከናውን ለማድረግ ተከታታይ ሥራዎች
እየተሰሩ መሆኑን መረጃው ጠቅሶ ፣ “ተጨማሪ ሥራዎች” ያላቸውን ስራዎች ግን ከመግለጽ ተቆጥቧል፡፡ በሚሊየን ዶላር ወጪ በአዲስአበባ ከተማ የተተከሉት እነዚሁ ዘመናዊ ካሜራዎች ዋንኛ ጥቅማቸው ኢህአዴግ መራሹ መንግስት ዜጎችን ለመሰለል ካለው ጥልቅ ፍላጎት ጋር የተያያዘ መሆኑን በመግለጽ መንግስት ለሕዝብ የሚያስብ ቢሆን ኖሮ ገንዘቡን ድህነትንና የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ ባዋለው ነበር ሲሉ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃውሞ አሰምተው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በተያያዘ ዜና ፌዴራል ፖሊስ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ በመታገዝ የሚፈጸሙ የሳይበር ወንጀሎችን ለመከታተልና
አጥፊዎችን ለመያዝ ቢሮ ከፍቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቋል፡፡ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ(ICT) በመደገፍ የሚሰሩ ወንጀሎች(ሳይበር ክራይም) አሳሳቢ እየሆኑ በመምጣታቸው ወንጀሎችን ለመከታተል፣ለመመርመርና ለማጣራት፣አጥፊዎችንም ለፍርድ ለማቅረብ በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ዘርፍ በፎረንሲክ ዳይሬክቶሬት ስር የሳይበር ላብራቶሪ ተቋቁሟል፡፡ላብራቶሪውም በሰለጠኑ ባለሙያዎች መደራጀቱን የፖሊስ መረጃ ጠቁሟል፡፡

አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ የፖሊስ መኮንን መንግስት በኢንተርኔት በሚደረጉት ትግሎች ተደናግጧል፣ በአገሪቱ  የለውጥ ፍላጎት እያየለ መምጣቱ አስደንግጦታል። በዚህም የተነሳ ሁሉንም ነገር ለመቆጣጠር ይፈልጋል ብለዋል።

    Thursday, 13 December 2012

    የሕግ ቅድስና ሆይ ወዴት ነሽ




                                                             www.ethiopiansemay.blogspot.com

                                                                  ከወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን (ጋዜጠኛ ) 
                                                                  የምፅአቷ ቀን ግም ያለች እንደሆን፣
                                                                  የነፍስ ዛንዚራን፣ የህይወት ብረት መዝጊያ…
                                                                  አድኖም-አያድን፤
                                                                  ሱባዔም አያግዝ፣ ሥጋ-ወደሙ አይሆን፣
                                                                  አሁን ነው ንስሐ፣ አሁን ነው መፀለይ፣
                                                                  ዛሬ ነው መመነን፤
                                                                  አሉ- አሉ መምህሩ
                                                                  የነፍስ ልጃቸውን ሲመክሩ-ሲዘክሩ፡፡
                                                                  - ታምራት ላይኔ
                                                                  የቀድሞው ም/ጠ/ሚ/ር ታምራት ላይኔ “ስኳር በመላስ” ተከስሰው
                                                                  እስር ቤት ከገቡ ከአምስት ዓመት በኋላ ማለትም በ1994  ዓ.ም
                                                                 የሕግንና የፍትህ ሥርአትን ምንነት በጥልቀት የሚፈትሽየመከራከሪያ ፅሁፍ
                                                                  ለጠቅላይ ፍርድ ቤት አቅርበው ነበር፡፡ ይህንን 
                                                        መከራከሪያቸውን“ዜጋ” መፅሔት በታህሳስ/ጥር 1994 ዓም ዕትሙ
                                                                 “ሲቀብሩ ብትደርስ አፈር ለግስ”  የሚል ርዕስ ሰጥቶ ለንባብ
                                                                  አበቃው፡፡ ያንን የአቶ ታምራት የመሟገቻ ፅሁፍ በርካታ የሕግ
                                                                  ባለሙያዎች ለሰነድነት ይፈልጉት እንደነበርም አስታውሳለሁ፡፡

    Wednesday, 12 December 2012

    ከአእምሮ ባርነት ነጻ እንውጣ!


    (መክብብ ማሞ)

    emancipation from mental slavery
    ከአእምሮ ባርነት ነጻ እንውጣ
    የሰውን ልጅ “ሰው” ከሚያሰኙት መካከል ማንነቱን የሚወስኑት የአካላዊ፣ የአእምሯዊና የመንፈሣዊ ኃይላት ውጤት መሆኑ በዋንኛነት ተጠቃሽ ነው፡፡ እነዚህ ዕድገታቸውን በተመጣጠነ መልኩ ካልተጠበቀ የሰው ልጅ “ሰው” ተብሎ ቢጠራና ራሱንም “ሰው ነኝ” እያለ ቢኖርም ከ“ሰው”ነት ተራ የወጣ ለመሆኑ ራሱ ምስክር ነው፡፡
    የእነዚህ ኃይላት ተመጣጥነው አለማደግ ሰውን ለብዙ ዓይነት ችግር ይዳርጉታል፡፡ ተምሮ ለድንቁርና፤ ባለጸጋ ሆኖ ለመንፈሣዊ ድህነት፤ ነጻ ሆኖ ለባርነት፤ … ይዳርጉታል፡፡ ከባርነትም የአእምሮ ባሪያ መሆን ትልቁ ጭቆናና ውርደት ነው፡፡

    Tuesday, 11 December 2012

    ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የ50 ሺ ብር ዋስ እንዲያቀርብ ታዘዘ

    ታህሳስ ፪(ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
    ኢሳት ዜና:-የፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 16ኛ ወንጀል ችሎት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በ50 ሺ ብር ዋስ በማስያዝ ክሱን በውጭ ሆኖ እንዲከራከር ትእዛዝ አስተላልፎአል።
    ዳኛው በመዝገብ ቁጥር 123 ሺ 875 የተከሰሰው ጋዜጠኛ ተመስገን ከዚህ ቀደም ለብይን ተቀጥሮ እያለ አቃቢ ህግ ክሱን በማንሳቱ የተቋረጠ ቢሆንም አቃቢ ህግ እንደገና ክሱን በመቀስቀሱ ነው ለዛሬ የተቀጠረው ብሎዋል። የአቃቢ ህግን የክስ አስተያየት ያዳመጠው በዳኛ አይሸሹም ሽመልስ የተሰየመው ችሎት ጋዜጠኛ ተመስገን  ደሳለኝ በ50 ሺ ብር ዋስ አልያም እስር ቤት ወርዶ ክሱን እንዲከራከር ውሳኔ አስተላልፎአል። የፍትህ ጋዜጣ አሳታሚ ድርጅት ተወካይም በሚቀጥለው ጊዜ ቀጠሮ እንዲቀርቡ በፖሊስ መጥሪያ እንዲደርሳቸው ውሳኔ አሳልፈዋል። የሚቀጥለው ጊዜ ቀጠሮም ለታህሳስ 24 ቀን 2005 ዓም ጠቃት ተቀጥሯል።

    የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቆች የሆኑት አቶ አምሀ እና አቶ ስሜነህ ፍርድ ቤቱ የፌደራል አቃቢ ህግ በፈለገው ጊዜ  መክሰስና ክሱን ማንሳት ስልጣን እንዳለው ብናውቅም ፣ ነገር ግን ዜጎችን ሰላማዊ ስራቸውን እየሰሩ እና እየኖሩ ሳለ በፈለገው ጊዜ ከሶ በፈለገው ጊዜ ክሱን በማንሳት ዜጎችን ማጉላላት የለበትም ፣ ስለዚህ ደንበኛችን ሲከሰስም ሆነ ዋስትና አስነፍጎት ካሳሰረ በሁዋላ ኪሱን አቋርጦ ሲፈታ ምንም ምክንያት ያልገለጸ ሲሆን ምክንያቱን እንዲያስረዳልን ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

    Monday, 10 December 2012

    “በአገራችን የአሸባሪዎች ድር አለ”

    ኃ/ማርያም የኢትዮጵያ ሙስሊም ቁጥር 35% ነው አሉ
    aljazeera and hailemariam

    ኢትዮጵያን መምራት ከጀመሩ ሶስት ወር ያስቆጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ በአሸባሪዎች የተከበበች አገር መሆኗን አመለከቱ። ኦብነግ በመገንጠል ስም የፖለቲካ ንግድ የሚያካሂድ ድርጅት እንደሆነ ገለጹ። መንግስታቸው ለሚታማበት ጉዳይ ማስተባበያ አቀረቡ።

    ከአልጃዚራ ቴሌቪዥን እንግሊዝኛው ክፍለጊዜ ጋር ቃለ ምልልስ ያካሄዱት አቶ ሃ/ማርያም ስለ አሸባሪዎች የተናገሩት በአገሪቱ የተነሳው የእስልምና ሃይማኖት ጥያቄና ተቃውሞ ስለቀረበበት የአህባሽን አስተምሮ ተከትሎ ከአያያዝ ጉድለት ጉዳዩ ወደ ቀጠናው እንዳይሸጋገር ስጋት ስለመኖሩ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ ነው።

    “ጥያቄው የጥቂቶች ነው” በሚል አቃለው በማቅረብ ማብራሪያቸውን ጀመሩ። መንግስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ እንደማይገባ በማመልከት አብዛኞቹ ሙስሊሞች ጥያቄያቸው የአስተዳደርና የሲስተም መሆኑንን አመላክተው ማንም ያልደፈረውን ጉዳይ አነሱ።ኢትዮጵያ የበርካታ ሃይማኖቶች አገር መሆኗን በመጥቀስም የአኻዝ መረጃ ሰጡ።

    Tuesday, 4 December 2012

    በኬኒያ የስደት “ኬዝ” ጋገራ





    ሰላም ወዳጄ እንዴት ሰነባበቱልኝ…!?
    ይቺ ጨወታ ለአዲሳባዋ ፍትህ (አዲስ ታይምስ) ተልካ ነበር። ታድያ እርስዎስ ለምን ታመልጥዎታለች!?
    ዛሬም ወደ ኬኒያ ይዤዎት ልሄድ ነው። “አረ አንከራተትከን!” ብለው ቅር እንዳይሰኙብኝ ጥሩ ጥሩ ጨዋታዎች ስላሉ እንዳያመልጥዎ ብዬ ነው።
    ኬኒያ ዘልቀን ከመግባታችን በፊት ስለ ሀገራችን ጉዳይ አንድ አስተያየት ለመስጠት ተነሳሽነቱ አለኝ። እኔ የምለው የአቡነ ጴጥሮስ ሀውልት ሊፈርስ ነው የሚለው ነገር የምር ነው ማለት ነው። መንግስታችን መቼም ማፍረስ ብርቁ አይደለም። እውነቴን ነው የምለው ላለፉት ከሃያ የሚበልጡ አመታት በሳቅ ሲያፈርሰን አይደል እንዴ የከረመው…!? አሁን ደግሞ ሀውልታችንን ሊያፈርስው መሆኑን ስንሰማ ባለፈው ጊዜ ልምዱ ነው ወይስ አዲስ ስልጠና ወስዶ ነው ብዬ ጠይቄያለሁ!
    ሎሬት “ኦቦ” ፀጋዬ ገብረ መድን ጉዱን አላየ ያኔ በርሱ ጉርምስና ዘመን አንድ ጀብራሬ ሀውልቱ ጥግ ሽንቱን እየሸና “አንተ ድንጋይ እሸናብሃልሁ… ጓደኞችህ የተባሉትን እሺ ብለው በማርቸዲስ ሲንፈላሰሱ አንተ ይኸው እምቢ ብለህ ድንጋይ ሆነህ ቀረህ! እሸናብሃለሁ” ሲለው ከጀብራሬው ጋር “ድንጋይ አይደለም አትሸናበትም” እያለ እንዳልተፋለመ፤ አሁን የባሰባቸው ጀብራሬዎች ሀውልቱን ሊያፈርሱት መሆኑን ቢሰማ ቢኖርም በብስጭት መሞቱ አይቀርም ነበር። አንድ የፌስ ቡክ ወዳጃችን “ፀጋዬ ይቺን ሰዓት” ስትል ሸጋ ግጥም ገጥማ ተመልግቻለሁ… እኔም አቅም አጥቼ እንጂ ይሄንን ሳይ ግጥም ብቻ ሳይሆን ቡጢም ብጋጠም ደስታዬ ነበር… ግን ፈራሁ…! እሸሸግበት ጥግ አጣሁ! እፀናበት ልብ አጣሁ… “ባከሽ እመብርሃን ይብቃሽ፣ ባክሽ ምስለ ፍቁር ወልዳ… ፅናት ስጪኝ እንድካፈል የእናቴን የኢትዮጵያን ፍዳ፣ ከነከሳት መርዝ እንድቀምስ ከነደደችበት እቶን የእርሷን ሞት እኔ እንድሞታት፣ ገላዋ ገላዬ እንዲሆን።… አዎን፣ ብቻዬን ነኝ ፈራሁ እፀናበት ልብ አጣሁ።…” ብለው ለሀገራቸው የተሰዉ አባት ሀውልት ሲፈርስ ማየት እውነትም ግጥም ብቻ ሳይሆን ቡጢም ያጋጥማል….!

    በስደት የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር አባላት አስተባባሪ ኮሚቴ Coordinating Committee of Exiled Members of Ethiopian Teachers Association




    የተሰጠ መግለጫ
                                                                                                                                ሕዳር 24, 2005 ዓ.ም

    የሙስሊም ወገኖቻችንን የመብት ጥያቄ ጥላሸት መቀባት በእሳት መጫወት ነው ። 
     

    “ይሉሽን በሰማሽ ገበያ ባልወጣሽ” እንዲሉ ወያኔ/ኢሕአዴግ በመንግስት ስም ሥልጣን ላይ ተቀምጦ በድርጅትም በግልም ነፃነቴ ይከበር ፣ ነፃነቴ አይደፈር ፣ ንብረቴ አይዘረፍ ፣ እትብቴ የተቀበረበት መሬት ለባዕድ አገር ከበርቴ አይሸጥብኝ፣ የዕምነቴን ሥርዓት በነፃነት ላከናውን….ወዘተርፈ የሚለውን ሁሉ ሽብርተኛ በሚል የሀሰት ውንጀላ ለስቃይና ለመከራ ሲዳርግ ቆይቷል። አሁንም ቀጥሎበታል። የኢትዮጵያ መምህራንና ማህበራቸው ኢመማ ይሕን  ለመሰለው የወያኔ የሀሰት ክስና ውንጀላ ሥርዓት ፣የአዳፍኔ (የአባይ) ምስክርነት፣ የፍርደገምድል ዳኝነት፣ ከዚሁ ጋር ተያይዞም እስራትና ግድያም ሰለባ የሆኑት ገና በጧቱ ነበር። ያኔ ሕብረተሰቡ ውዥንብርና መጠራጠር ውስጥ ሊገባ የተገደደ መስሏል። ውሎ እያደረ ግን የወያኔ/ ኢሕአዲግ ማንነትና ምንነት በሂደት ቁልጭ ብሎ ታይቷል። የዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችንም ሆነ ራሱ በተግባር ለማዋል በሰነድነት ይዤዋለው የሚለውን ሕገ መንግሥት ተብዬ ሰነዱን ጎዝጉዞ ተቀምጦበታል። በአንዳንድ ወገኖቻችን እንደተጠቀሰው ሕገ መንግሥት ተብዬው የውሽት ሰነድ “ሕገ አራዊት” መሆኑ ማረጋገጫው ይህ ቡድን ለመብቴ እቆማለሁ ያሉትን ሰዎች እያደነ ማሰሩ፣ ማሰቃየቱ፣ ንብረት መዝረፉና ከዚያም በላይ ግድያ መፈጸሙ ነው።

    Saturday, 1 December 2012

    ከፍተኛ ሙስና ፈጽመዋል የተባሉት ግለሰብ የኦሮምያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው ተሾሙ


    ኢሳት ዜና:-የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ጉባኤውን ሲያጠናቅቅ የ77 ዳኞችን ሹመት አጽድቋል።የክልሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ ፍቅሩ አያና ከምክር ቤት አባላቱ ከፍተኛ የሆነ ተቃውሞ ቢቀርብባቸውም፣ ከፍተኛ አመራሮች ስለፈለጉዋቸው ብቻ እንዲሾሙ መደረጉን የኦህዴድ ምንጮች ገልጸዋል።ህዳር ፳፪ (ሃያ ሁለት) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም የምክር ቤት አባላት በአቶ ፍቅሩ ላይ ካቀረቡዋቸው የመቃወሚያ ሀሳቦች መካከል ግለሰቡ በሙስና የተዘፈቁ ናቸው፣ በዞናቸው ዳኛ ሆነው በሰሩበት ወቅት በህዝብ የተጠሉና ህዝብን ያንገላቱ ናቸው፣ የስነምግባር ችግር አለባቸው፣ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም የሚሉት ይገኙበታል። የክልሉ ባለስልጣናት ከምክር ቤት አባላት ለቀረበባቸው ተቃውሞ አጣርተን መልስ እንሰጣለን የሚል ድፍንፍን ያለመልስ በመስጠት ሹመቱ እንዲጸድቅ አድርገዋል።
    የምክር ቤት አባላቱ በባለስልጣኑ አሰራር ላይ ነቀፌታ ሲያቀርቡ እንደነበር ታውቋል። በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ክልሉን ፕሬዚዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳን ጨምሮ የስራ አስፈጻሚዎች የስልጣን ሹም ሽር ይኖራል የሚል አጀንዳ ተይዞ የነበረ ቢሆንም ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ሁኔታ አጀንዳው እንዲሰረዝ ተድርጓል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አቶ አለማየሁን ለመተካት ሀሳብ ቢቀርብም በሚተካው ሰው ላይ የስራ አስፈጻሚዎች ለመስማማት ባለመቻላቸው እንዲቀር ተድርጓል። አንዳንድ የስራ አስፈጻሚ  አባላት ስብሰባ ረግጠው እስከመውጣት መድረሳቸውን ለማወቅተ ችሎአል። በሰሞኑ የምክር ቤት ስብሰባ ላይ አርብ እለት ከተገኙት ከምክትል ፕሬዚዳንቱ ከአቶ አብዱላዚዝ በስተቀር ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት በማጠቃለያው ጉባኤ ላይ አልተገኙም። ሰሞኑን ለአቶ ሙክታር ከድር የተሰጠው የምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትርነት ቦታ በተወሰነ መጠን በምክር ቤቱ ውስጥ ይነሳል ተብሎ የተጠበቀውን ተቃውሞ ማብረዱ ታውቋል።

    የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ክስ እንደገና ተቀሰቀሰ

    ኢሳት ዜና:-የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከዚህ ቀደም በፌዴራል ዐቃቤ- ሕግ ቀርቦበት የነበረው ክስ እንደገነ ተቀሰቀሰ፤

    ትላንት ሃሙስ ህዳር 20 ቀን 2005 ዓ.ም ከቀትር በኋላ ወደ ጋዜጣው ቢሮ የፍርድ ቤት መጥሪያ ይዘው የመጡት የፖሊስ አባላት ጋዜጠኛ ተመስገን ከአዲስ አበባ ውጪ መሆኑ ተነግሯቸው ተመልሰዋል ። ዓርብ ህዳር 21 ቀን 2005 ዓ.ም ከሰሃት በኋላ የፌዴራል ፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 16ተኛ ወንጀል ችሎት ጋዜጠኛ ተመስገን በሌለበት ችሎት የሰየመ ሲሆን የፍርድ ቤት መጥሪያ ለጋዜጠኛው ሊያደርሱ የሄዱት ፖሊሶች በጊዜው ሊያገኙት አለመቻላቸውንና ለሥራ ባልደረቦቹ ግን መንገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን የዋስትና መብት የነፈጉት ዳኛ መጥሪያው እንዳልደረሰው ካረጋገጡ በኋላ ዐቃቤ- ሕግን የውሳኔ አስተያየት የጠየቁ ሲሆን ዐቃቤ- ሕግ በበኩሉ በቀጣይ እንዲቀርቡልኝ ማዘዣ ይጣፍልኝና አጭር ቀጠሮ ይሰጠኝ ብሏል፡፡

    የችሎቱ ዳኛ በበኩላቸው የፍርድ ቤት መጥሪያ ለፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝ እና ለድርጅቱ ጠበቃ እንዲደርስ ማዘዣ እንዲወጣ አዘው ቀጣይ ቀጠሮውንም ለታህሳስ 2 ቀን 2005 ዓ.ም ጊዜ ቀጠሮ ሰጥተዋል፡፡ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ  ከጤናው ጋር በተያያዘ ወደ አዋሳ መጓዙን ተከትሎ መጥሪያ እንደደረሰው ለኢሳት ገልጿል። የፕሬስ አፈናው በአቶ ሀይለማርያም የስልጣን ዘመንም ተጠናክሮ መቀጠሉን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በአዲስ ታይምስ መጽሄት ላይ ሲሰራ የገጠመውን ችግር በመዘርዝር ገልጿል ተመስገን ፍትህ ጋዜጣን ሲያሳትም በነበረበት ወቅት ከ39 ባላነሱ እንያንዳንዳቸው ከ106 በላይ ዝርዝር ክሶችን በያዙ ወንጀሎች መከሰሱ ይታወቃል። ከታዋቂው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ጋር በፕሬስና በወቅታዊ የአገራች ፖለቲካ ዙሪያ ያደረግነውን ቃለምልልስ ከዜናው በሁዋላ በትኩረት ክፍለ ጊዜ የምናቀርብ መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን።