May 27, 2014
ከፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማርያም
ትርጉም በነጻነት ለሀገሬ
እ.ኤ.አ ሜይ 2/2014 ቢቢሲ/BBC እንደዘገበው በኢትዮጵያ በስልጣን ላይ እንደመዥገር ተጣብቆ የሚገኘው ገዥ አካል የጸጥታ ኃይሎች ከመናገሻ ከተማዋ ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ በኩል በ80 ማይሎች ርቀት ላይ በምትገኘው የአምቦ ከተማ ላይ ቢያንስ 47 የዩኒቨርስቲ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን በአሰቃቂ ሁኔታ በጥይት ኢሰብአዊ በሆነ መንገድ ረሽነዋል፡፡ ስብዕናው በውሸት እና በሀሰት ውንጀላ የበከተው ገዥ አካል ይህንን እልቂት እንደተለመደው ሽምጥጥ አድርጎ በመካድ “ጥቂት ጸረ ሰላም ኃይሎች በቆሰቆሱት እና በአስተባበሩት አመጽ“ ምክንያት የሚል የሀሰት ፍረጃ በመስጠት በግፍ የተገደሉትን ወገኖቻችንን ቁጥር ለማሳነስ ጥረት አድርጓል፡፡ ይህ በወጣት ተማሪዎች እና ህጻናት ላይ የተፈጸመው የማንአለብኝነት የእብደት አሰቃቂ እልቂት በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ዘንድ ሰፊ ሽፋን አልተሰጠውም፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች/HRW የተባለው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት “በአምቦ፣ በነቀምት፣ በጅማ እና በሌሎች ከተሞች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ባሰሙት ንጹሀን ዜጎች ላይ እየተፈጸመ ያለው ግድያ እና ድብደባ ይቁም“ የሚል መግለጫ በማውጣት እኩይ ድርጊቱን አውግዟል፡፡ እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች ዘገባ “በኦሮሚያ የሚገኙ ከ15 በላይ የሚሆኑ ህብረተሰብ አቀፍ ገጠራማ እና ከተማ ቀመስ አካባቢዎችን ወደ አዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት የወሰን ክልል የሚያካትተው እና የኦሮሞ አርሶ አደሮችን እንዲሁም ሌሎች ኗሪዎችን የሚያፈናቅለው የአዲስ አበባ የተቀናጀ መሪ የልማት ዕቅድ ሀሳብ ተዘጋጅቶ ይፋ መሆኑን ተከትሎ የተማሪዎች የተቃውሞ አመጽ ገነፈለ“ ብሏል፡፡ በማስከተልም ሂዩማን ራይትስ ዎች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሟቸውን ባሰሙት ተማሪዎች ላይ የገዥው አካል የጸጥታ ኃይሎች እየወሰዱ ያሉትን የኃይል እርምጃ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ጠይቋል፡፡
በዚህ መረን በለቀቀ ዕኩይ ድርጊት የተሰማኝን ሀዘን በቃላት ለመግለጽ ተስኖኛል ምክንያቱም ልብን ሰብሮ የሚገባው ይህ የአሰቃቂ እልቂት ሀዘን ልሸከመው ከምችለው ከአቅሜ በላይ ሆኖብኛልና፡፡ የብሩህ አዕምሮ ባለቤት እና የነገይቱ ኢትዮጵያ ተረካቢ የሆኑት እምቦቀቅላ ተማሪዎች ገና በወጣትነት ለጋ እድሚያቸው ኃላፊነት በማይሰማው መንግስት ነኝ ባይ የወሮበላ ቡድን ስብስብ በጥይት ውርጅብኝ በመጨፍጨፋቸው ታላቅ ሀዘን ተሰምቶኛል፣ እንዲሁም ቀጣይነት ባለው መልኩ ስሜቴን እየቆጠቆጠኝ ይገኛል፡፡ ተማሪዎቹ የሚሰማቸውን ቅሬታ በሰላማዊ መንገድ ለማቅረብ ህገመንግስታዊ ያልተገደበ መብት ነበራቸው፡፡ ያንን መብት በመጠቀም በሰላማዊ መንገድ ወደ አደባባይ በመውጣት ተቃውሟቸውን በማሰማታቸው ምክንያት ብቻ የጥይት በረዶ ተርከፍክፎባቸዋል፡፡ እናም ሁላችንም ልናዝንላቸው ይገባል፡፡ ኃላፊነት በጎደለው ገዥ አካል በተፈጸመው እልቂት ምክንያት የምርጥ እና የባለብሩህ አእምሮ ባለቤት የነበሩትን ወጣቶች ኢትዮጵያ በማጣቷ አጅግ በጣም ለኢትዮጵያ አዝናለሁ፡፡ የእልቂቱ ሰለባ ለሆኑት ወጣቶች ወላጆች እና ጓደኞች የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ መጽናናትን እንዲሰጣቸውም ለኃያሉ አምላክ ጸሎቴን አደርሳለሁ፡፡