August 12, 2015
በኤልያስ ገብሩ
- ታገሉ! ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ (ከዝዋይ እስር ቤት)
- ተመስገን ደሳለኝ ስለሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ፍርድም ሀሳቡን ሰንዝሯል
ቦሌ አካባቢ ብርዱ ጠንከር ያለ ነበር፡፡ ከቦሌ ብራስ ወደሚሊኒየም አዳራሽ በሚወስደው ቀጭን መንገድ ላይ ወንዱም ሴቱም በፍጥነት ይራመዳል፡፡ ከታክሲ በሁለቱም አቅጣጫዎች የወረዱ ሰዎች ወደመደበኛ ሥራቸው ለመግባት ብሎም የግል ጉዳያቸውን ለመፈጸም ሲንቀሳቀሱ ነበር – ከትናንት በስትያ ሰኞ (ነሐሴ 04 ቀን 2007 ዓ.ም) ጥዋት 1፡45 ሰዓት፡፡
እኔ እና ወዳጄ አቤል ዓለማየሁ ወደከአዲስ አበባ 160 ኪሎ ሜትር ርቀት ወደሚገኘው ዝዋይ እስር ቤት አምርተን ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬን እና ተመስገን ደሳለኝን ለመጠየቅ በዚህ ቀን ቀጠሮ ይዘን ነበር፡፡ አቤል ከቀጠሯችን 20 ደቂቃ ዘግይቶ፣ ቦሌ ጫፍ ደረሰና ወደቃሊቲ መናሃሪያ ሁለት ታክሲዎችን በመጠቀም ደረስን፡፡ ወደዝዋይ የሚጭኑ ሚኒባስ ታክሲዎች እና ‹‹አባዱላ/ዶልፊን›› የሚል መጠሪያ የተቸራቸው የህዝብ ማመላለሻ መኪኖች ቢኖሩም በተለምዶ ‹‹ቅጥቅጥ›› የሚባለውን መካከለኛ አውቶቡስ ምርጫችን አደረግን – የትራፊክ አደጋን በመስጋት፡፡
የተሳፈርንበት አውቶቡስ፣ ከቃሊቲ ትንሽ ወጣ ካለ በኋላ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ በእስር ላይ የሚገኙትን የግንቦት 7 ዋና ፀሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ “ልማቱን አሳዩኝ” ሲለን ከከተማ ወጣ እያደረግን የምነሳየው… [እውነት ግን፣ በከባድ እስር ላይ መሆናቸው የሚገመተው አቶ አንዳርጋቸው ‹ልማቱን አሳዩኝ› ይሏቸዋልን?!]›› ሲሉ ለቪኦኤዋ ጋዜጠኛ ትዝታ በላቸው የገለጹትን፣ የአዲስ አበባ አዳማ አዲሱ የፍጥነት መንገድ (Express way)ን ተቀላቀለ፡፡ በዚህ መንገድ ሁለታችንም ሄደን አናውቅም ነበር፡፡ ሆኖም እስከዛሬ ካየኋቸው የመኪና መንገዶች በደረጃው ከፍ ያለ ይመስላል፡፡ [በሀገራችን አምረው የተሰሩ የመኪና መንገዶች በጥቂት ዓመታት ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የመቦርቦር፣ የመፈረካከስ፣ ውሃ የማቆር ችግሮች ገጥሟቸው እንዲሁም ከመንገዱ ዳር እና ዳር የሚገኙ የብረት አጥሮች ተሰርቀው፣ ተገጭተው፣ ተጨረማምተው፣ ተነቃቅለው … አደጋ ሲያደርሱና የተለመደ የሬንጅ የመለጠፍ ሥራ ሲሰራላቸው በገሃድ የምናየው ሀቅ መሆኑን ማስታወስ ግን የግድ ይላል] ይሄኛው መንገድ ከጠቀስኳቸውና ካልጠቀስኳቸው ችግሮች ምን ያህለ ነጻ ነው? ለሚለው ትክክለኛ መስክርነት መስጠት ያለበት ለእውነት የቆመ የዘርፉ ባለሙያ ቢሆንም በኢህአዴግ ‹ልማት› ላይ የጥራት መተማመኛ ማግኘት እጅግ ከባድ መሆኑን ግን አምናለሁ፡፡ አስፋልቱ ለፍጥነት አመቺ መሆኑን ግን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡
በሶስት ሰዓታት ጉዞ ዝዋይ በመድረስ ምሳ ከበላን በኋላ ወደእስር ቤቱ የፈረስ ጋሪ መጠቀም ግዴታችን ነበር፡፡ አቧራማው አስቸጋሪ መንገድ፣ ከፊሉ ደቃቅ አሸዋ መልበስ ጀምሯል፡፡ የእስር ቤቱ የማስፋፊያ ግንባታ ሥራ፣ በፊት ውብሸትን ለመየጠቅ ስመጣ ከማውቀው ተፋጥኗል፡፡ አንዱ የሥርዓቱ “የልማት ውጤት” እስረኛ ማብዛት አይደለ ታዲያ?!