Friday, 30 November 2012

የድምጻችን ይሰማ የኮሚቴ አባላት ፍርድ ቤት ቀረቡ


ኢሳት ዜና:-የሙስሊም ኢትዮጵያውያንን ሰላማዊ ተቃውሞ በመምራታቸው በሽብርተኝነት ተከሰው በእስር ላይ የሚገኙት የድምጻችን ይሰማ የአመራር አባላት ዛሬ ልደታ በሚገኘው ከፍተኛው ፍርድ ቤት ቢቀርቡም ለህዳር 27 ቀን 2005 ዓም የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ወደ እስር ቤት ተመልሰዋል።

የኮሚቴ አባላት ጠበቃ የሆኑት አቶ ተማም አባቡልጋ ለኢሳት እንደገለጡት የዛሬው ችሎት አቃቢ ህግ በጠበቆች በኩል ለቀረበው መቃወሚያ መልስ ለመስጠት  ተብሎ የተቀጠረ ነበር። አቃቢ ህግ መልሱን በንግግር ለፍርድ ቤት ማቅረቡን የገለጡት አቶ ተማም ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን መከራከሪያ ሰምቶ ተከሳሾች በቀረበባቸው ክስ ቃላቸውን ይስጡ አይስጡ በሚለው ላይ ውሳኔ ለማስተላለፍ የፊታችን ሀሙስ መቀጠራቸውን ተናግረዋል።

አቶ ተማም እንዳሉት ፍርድ ቤቱ በመጪው ሀሙስ ክሱ እንዲቀጥል፣ እንዲሻሻል፣ ወይም ውድቅ እንዲሆን ብይን ይሰጣል። ጠበቆች ባለፈው ሳምንት ባቀረቡት መቃወሚያ በአቃቢ ህግ የቀረበው ክስ ህገመንግስቱን የጣሰና በርካታ የህግ እጸጾች ያሉበት ነው በማለት መገልጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለኮሚቴ አባላቱ ድጋፋቸውን ለመስጠት ወደ ልደታ ያቀኑ ሙስሊሞች በፖሊሶች መባረራቸውን አንዳንዶችም በፖሊስ መኪኖች ተጭነው መወሰዳቸው ታውቋል።

ጉዳዩን በማስመልከት በአካባቢው የነበሩ የተለያዩ የእስልምና እምነት ተከታዮችን አነጋግረን እንደተረዳነው ፖሊሶች እናቶችን ብቻ በመለየት እየደበደቡ ወደ እስር ቤት ውሰደዋቸዋል ሌላ ሙስሊም  በበኩሉ ” ወንዶችን ቢደበድቡ የተለመደ ነው፣ እናቶችንና እህቶቻችንን መደብደባቸው ግን ሊወጥልን አልቻለም” ብሎአል የሙስሊም  ትዮጵያውያን ተቃውሞ እንደቀጠለ ባለበት በዚህ ጊዜ መንግስት፣ ኮሚቴ አመራሩን የሚያወግዙ ሰልፎችን በተለያዩ ከተሞች እያዘጋጀ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል። በኦሮሚያ ክልል አዳማን ጨምሮ በተለያዩ ዋና ዋነ ከተሞች ለማዘጋጀት የኮሚቴ አባላት መዋቀራቸውን ለማወቅ ተችሎአል።

አሁንም የተሃድሶ ያለህ!!!


(ርዕሰ አንቀጽ)

intellectual reform
“አንድነትን ስንመሰርት በቅንጅት ወቅት ስለሰራነው ጥፋትና የፖለቲካ ስህተት የገመገምነው ነገር የለም” ዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማርያም አንድነት ፓርቲን ከቅንጅት ጋር በማነጻጸር ከተናገሩት፡፡ በኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፓርቲና ድርጅቶች መዋቅራዊ ጥንካሬና ደጋፊዎቻቸውን አስተባብረው ውጤት ስመዝገብ ያለመቻላቸው ጉዳይ አነጋጋሪ ነው። ተቃውሞ በኢትዮጵያ በፓርቲ መሪዎችና በገዢው ኢህአዴግ መካከል የሚደረግ እሰጥ አገባ ካልሆነ በስተቀር በደጋፊዎች ተሳትፎ ገዢውን ፓርቲ የማስገደድና እጁን የመጠምዘዝ ደረጃ ላይ ደርሶ ሊታይ አልቻለም።  ከቅንጅት መፈራረስና ልዕልናው መክሰም ጋር የህዝብ ስሜትም አብሮ ተዳፍኗል የሚለው አስተያየት ሚዛን የደፋ የሚሆንባቸው የበዙት ለዚሁ ነው። በድርጅት ደረጃ ችግሩን ተመልክተው ስለመታደስ የሚያስቡ ስለመኖራቸው ግን ለረዥም ጊዜ አልሰማንም።

በኢትዮጵያ ህዝብን ለትግልና ለእምቢተኝነት የሚያነሳሱ ጉዳዮች ሞልተው የፈሰሱ ቢሆንም ህዝብ በስርዓቱ ከመበሳጨት የዘለለ እንቅስቃሴ አለማድረጉ ስርዓቱ ከዘረጋው የአፈና መዋቅር ጋር የሚያገናኙት ቢኖሩም በዋናነት የተቃዋሚዎች ድክመት ጎልቶ እንደሚታይ አሁን አሁን ይፋ እየሆነ ነው። በተለይም ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ሰሞኑን “የግል አስተያየቴ ነው” በማለት ያቀረቡት ጽሁፍ የችግሩ ቁልፍ ነውና ሁሉም ወገኖች አሰራራቸውን ሊፈትሹ እንደሚገባ ይሰማናል – አሁን!!

ህወሃት አረጋግቶ አገገመ


ብቸኛው ተቃዋሚ የንግድ ሚኒስትሩን ሹመት ኮነኑ

Assigned EPRDFist
ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ አገሪቱን በመሩበት ሶስት ወራት ካቢኒያቸውን በደንብ መገምገማቸውን በግምት በመግለጽ ተቃውሞ ያቀረቡት አቶ ግርማ ሰይፉ በምደባው በተወሰነ ደረጃ እንደሚስማሙ ተናግረዋል። የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔን ምደባ የተቃወሙት በማስረጃ ነው። የዓለም ባንክ ለንግድ ምዝገባ የማያመቹ አገሮችን ዝርዝር ጥናት ይፋ ሲያደርግ ኢትዮጵያ ከ185 አገሮች የ165ኛ ደረጃ ማግኘቷን፣ ለዚህም የዳረጉት ቀደም ሲል በተጠባባቂ ሚኒስትርነት ለረዥም ጊዜ ያገለገሉት አቶ ከበደ ጫኔ በመሆናቸው አዲሱ ሹመት እንደማይገባቸው አቶ ግርማ በተቃውሞ ተናግረዋል። በተጨማሪም ህዝብ የማወቅ መብት ስላለው ከፍተኛ ባለሥልጣናት ከሃላፊነታቸው ሲነሱ ምክንያቱ ይፋ ሊሆን እንደሚገባው ማሳሰቢያ አቅርበዋል።
አቶ ግርማ ብቻ የተቃውሞ አስተያየት ያቀረቡበት ምደባ በስፋት ሃሳብ ሲሰጥበት ለነበረው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ወንበር መልስ በመስጠት ተጠናቋል። ምደባውን ህወሃት ሲያሸንፍ የተመደቡት ሚኒስትር አቶ መለስ በህይወት እያሉ ይተኳቸዋል የተባሉት ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ናቸው። የግራ ዘመሙን የፖለቲካ ጎዳና እምብዛም የማያውቁት ዶ/ር ቴዎድሮስ “ልምድ ያላቸው ታጋይ አይደሉም” በሚል ህወሃትን በከፍተኛ አመራርነት ስለመወከላቸው ጥያቄ የሚያቀርቡባቸው ነበሩ።

Wednesday, 28 November 2012

መንግስት በመላ አገሪቱ ሙስሊሞችን እያስገደደ ለተቃውሞ ሰልፍ ሊያስወጣ ነው

ህዳር ፲፱ (አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም


ኢሳት ዜና:-ከኢህአዴግ ምንጮች የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙና መንግስት በሙስሊሙ ላይ በሚፈጽመው ኢሰብአዊ  ድርጊት የተነሳ ተቃውሞ ያስነሳሉ በተባሉ አካባቢዎች በሙሉ ፣ መንግስትን የሚደግፉ ሰልፎች ይደረጋሉ።

አብዛኛው ህዝብ ተገዶ እንዲወጣ፣ የድርጅት አባላት ከፍተኛ ተልእኮ እንደተሰጣቸው ለማወቅ ተችሎአል።
በዛሬው እለትም በቅርቡ የመንግስት ታጣቂዎች 4 ሰዎችን በገደሉበት ገርባ እና ደጋን መንግስትን የሚደግፉ ሰልፎች ተደርገዋል።

የሰልፉ ዋና አላማ በፍርድ ሂደት ላይ የሚገኙት የድምጻችን ይሰማ የሙስሊም ኮሚቴ አባላት አሸባሪዎች ናቸው የሚል መልእክት ለማስተላለፍ ነው።

ኢህአዴግ በኮሚቴ አባላቱ ላይ ለፍርድ ቤቱ ጠንካራ ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ በዳኞች ላይ ተጽኖ ለመፍጠር ማሰቡን የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

Tuesday, 27 November 2012

አላማጣ ታፍነው የተወሰዱ ከ20 በላይ ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም



ህዳር ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም


ኢሳት ዜና:-በራያና አዘቦ ፣ በአላማጣ ከተማ ከኤልክትሪክ መስመር መቃጠል ጋር በተያያዘ በጥርጣሬ የተያዙ ከ20 በላይ ግለሰቦች ወደ ማይጨው ከተማ ተወስደው መታሰራቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ቢናገሩም ፣ ዘመዶቻቸው እንዳይጠይቋቸው በመደረጉ ስለደህንነታቸው ሁኔታ ለማወቅ አልተቻለም።


ወጣቶች የታሰሩት ለኢንቨስተሮች ተብሎ የተዘረጋውን የኤልክትሪክ ምሰሶ አቃጥላችሁዋል በሚል ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጡት ታፍነው የተወሰዱት ወጣቶች በእስር ቤት ጉዳት ሳይደርስባቸው አልቀረም። በጉዳዩ ዙሪያ የመንግስት ባለስልጣናትን ለማናገር ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።በሌላ በኩል ደግሞ ስራ ለመቀጠር ወደ ጅጅጋ የሄዱ 9 ወጣቶች በፖሊስ ተዘርፈውና ተደብድበው ለልመና መዳረጋቸውን የአካባቢው ወኪላችን ገልጿል። ከባህርዳር ዩኒቨርስቲ የተመረቁት 9ኙ ወጣቶች የተነሱት ሞጣ እየተባለች ከምትጠራ በምስራቅ ጎጃም ዞን በምትገኝ ከተማ ሲሆን፣ ወደ ጂጂጋ ያቀኑትም ለመምህርነት ስራ ተወዳድረው በማሸነፋቸው ነው። መምህራኑ ወደ ምድብ ቦታቸው እስከሚሄዱ  ድረስ አልጋ ተከራይተው በመጠባባቅ ላይ ሳሉ፣ ሌሊት ፖሊሶች ወደ ክፍላቸው በመግባት ከ1600 እስከ 2000 ብር እንዲሁም የሞባይል ስልኮቻቸውን በድብደባ ቀምተዋቸዋል። ፖሊሶቹ ገንዘብ አልተወሰደብንም ብላችሁ ፈርሙ በማለት ካስፈረሙዋቸው በሁዋላ የመሳፈሪያ 50 ብር በመስጠት ሀረር ወስደው ጥለዋቸዋል። መምህራኑ ወደ አካባቢያቸው የሚመለሱበት የትራንስፖርት ገንዘብ ስላጠራቸው በአሁኑ ሰአት ሀረር ከተማ ውስጥ በልመና ላይ መሆናቸውን ወኪላችን ገልጿል።

በኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት አርማጭሆ ሳንጃ ወረዳ ልዩ ስሙ ጃንሱማ በተባለው ቦታ ወታደራዊ ጥቃት ፈጸመ


Ethiopian People Patriots Front - EPPF
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት በወያኔ ቅጥረኛና ምንደኛ የልዩ ሃይል ታጣቂ ቡድን ላይ የጀመረውን የማጥቃት ዘመቻ አጠናክሮ በመቀጠል ሕዳር 15-2005 ዓ.ም
አርማጭሆ ሳንጃ ወረዳ ልዩ ስሙ ጃንሱማ በተባለ ቦታ ባደረገው ውጊያ 14 የጠላት ወታደሮችን በመግደልና 12 በማቁሰል ከፍተኛ ወታደራዊ ድሎችን በማስመዝገብ ግንባሩ የተሰማራበትን ግዳጅ በድል እየተወጣ መሆኑን የግንባሩ ወታደራዊ መምሪያ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዘራፊውና ከነፍሰ-ገዳዩ የወያኔ አምባገነናዊ ገዥ ቡድን ለማላቀቅ ያለው ብቸኛ አማራጭ መንገድ በትጥቅ ትግል ስርዓቱን ማንበርከክ መሆኑን ጠንቅቆ ያወቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ሰራዊት ሀገርንና ወገንን ለመታደግ ቆርጦ በመነሳት በሰሜኑ የሐገራችን ክፍል ወታደራዊ ስትራቴጅውን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ ሰሞኑን አርማጭሆ ሳንጃ ወረዳ ልዩ ስሙ ጃንሱማ በተባለው ቦታ ባደረገው የማጥቃት ዘመቻ 26 የጠላት ወታደሮችን ሙትና ቁስለኛ በማድረግ ወታደራዊ የበላይነትን የተቀዳጀ ሲሆን፣ ከሞቱት 14 የልዩ ሃይል ታጣቂ ቡድን መካከል አበበ የሚባለው የቀራቅር ተወላጅና አለልኝ የሚባል የደባርቅ ተወላጅ የሆኑት ከፍተኛ አመራሮች መሞታቸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር ወታደራዊ መምሪያ ገልጿል።

በራስ አሉላ ስም የተሰየመው ት/ቤት በመለስ ተቀየረ


ከኢየሩሳሌም አርአያ

በትግራይ ተምቤን – አብዪአዲ የሚገኘውና በጀግናው ራስ አሉላ አባነጋ ስም ተሰይሞ የቆየው የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ስያሜው ተቀይሮ በመለስ ዜናዊ ስም እንዲሰየም መወሰኑን ታማኝ ምንጮች አስታወቁ።

በደርግ ዘመን የተሰራውና በራስ አሉላ ስም ተሰይሞ የ 9 – 10ኛ ክፍል ተማሪዎችን ተቀብሎ ሲያስተምር ከቆየ በሑላ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የት/ቤቱን አቅም ለማሳደግ በሚል የ11-12ኛ መመሪያ ክፍሎችን ለመገንባት በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የሚገኙ የአካባቢው ተወላጆች ገንዘብ አዋጥተው ስራው መከናወኑን ምንጮቹ ጠቁመዋል። ግንባታው ተጠናቆ ባለፈው ነሃሴ ወር ለማስመረቅ በዝግጅት ላይ እንዳለ አቶ መለስ በማለፋቸው ፕሮግራሙ መሰረዙን ሲታወቅ; ከሁለት ሳምንት በፊት በተከናወነው የምረቃ ስነ-ስርአት የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በስፍራው እንደተገኙ ማወቅ ተችሎዋል።