August 30, 2013
ከኢትዮጵያዊ ሙስሊም
እዚህ አሜሪካ ከዋሽንግተን ዲሲ ከተማ የሚሰራጨው የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ራዲዮ ጣቢያ በቅርቡ የሙስሊም ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ነፃነትና መብትን የማስከበር ሰላማዊ ትግልን ከ‹ፖለቲካዊ እስልምና› ጋር ለማያያዝ የሚቃጣ “የራዲዮ ዝግጅት” አቅርቧል፡፡ ዝግጅቱ ዊኪሊክስ በተሰኘው ድረ‑ገፅ አምና ይፋ የተደረጉ የስቴት ዲፓርትመንት ምሥጢራዊ ሰነዶችንና ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች ከተከሰቱ ግጭቶች ጋር የተያያዙ የድምፅ ግብዓቶችን በመጠቀም ወቅታዊውን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሃይማኖት ነፃነትን የማስከበር ሰላማዊ ትግል ከ‹ፖለቲካዊ እስልምና› ጋር በማያያዝ ጭቃ ለመቀባት፣ ብሎም ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖችን ግንዛቤ ለማዛባት ይሞክራል፡፡
ይህ ጽሑፍ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን እየተነዛና እየተሰበከ ባለው ጥላቻና ግጭትን የመቀስቀስ ዓላማ ያዘለ ፕሮፖጋንዳ አኳያ፣ ወቅታዊውን የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የሃይማኖት ነፃነትን የማስከበር ሰላማዊ ትግል በአጭሩ በማስቃኘትና፣ በአሁኑ ወቅት መንግሥትና አጫፋሪዎቹ እያካሄዱ ያሉትን ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት ያለመ ዕኩይ ዘመቻ አደገኛነት በማመላከት ዓላማ የተዘጋጀ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ራዲዮ ያቀረበውን ዝግጅት አሉታዊነት በድፍኑ ከመተቸት ይልቅ፣ በዝግጅቱ ይዘት ላይ ያተኮረ ሰፋ ያለ ሒስ ማቅረብ አስፈላጊ ይመስለናል፡፡ እናም በዚህ ጽሑፍ የራዲዮ ጣቢያው ባቀረበው ዝግጅት ይዘት ጥቂት አንኳር ጉዳዮች ላይ በማተኮር የጣብያውን አሳዛኝና አሳፋሪ ሥራ ለማስቃኘት እንሞክራለን፡፡