እሳት አስነሳችሁ በሚል እስሩ ቀጥሏል
በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ተቃውሞ ቢያቀርቡም የኢህአዴግን ጆሮ ማግኘት ያልቻሉ ተበዳዮች ርምጃ ወሰዱ። ሕዝብ ወዶና ፈቅዶ ያልተቀበለው ኢንቨስትመንት ከዘረፋ ተለይቶ እንደማይታይ የአካባቢው ነዋሪዎች አስታውቀዋል። ውድመት የደረሰበት የህንድ ኩባንያ በልማት ባንክ ላይ ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችል ስጋት አለ። ለደረሰው ጉዳት “ተጠያቂው ማን ነው?” የሚል ጥያቄ ተነስቷል። በጥርጣሬ የሚታሰሩ መበራከታቸው በክልሉ ባሉ ተመሳሳይ የእርሻ ኢንቨስትመንት ባለቤቶችን ስጋት ላይ ጥሏል።
ሻይ ቅጠል ለማልማት የተፈጥሮ ጥብቅ ደን እንዲያወድም የተፈቀደለት ቬርዳንታ ሀርቨስት የተባለ ኩባንያ በከፍተኛ ወጪ ያለማውና ለመለቀም በደረሰ ምርት ላይ ማንነታቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች እሳት ለቀውበታል። ጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓም ደረሰ በተባለው ቃጠሎ ኩባንያው የደረሰበት ሊሳራ እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ አስታውቀዋል።
አንጋፋ እድሜ ጠገብና ረዣዥም የተፈጥሮ ደን በመጨፍጨፍ ጣውላ እያመረተ ሲቸበችብ የነበረው ኩባንያ ሙሉ ንብረቱና ከፍተኛ መጠን ያለው የጣውላ ምርት ከተለያዩ ማሽኖች ጋር ወድሞበታል። የአካባቢው የጎልጉል ምንጮች እንዳሉት ኩባንያው ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ ለመሰብሰብ የደረሰውን የሻይ ቅጠል ማሳ አጋይቶታል።
በጋምቤላ ክልል በመዠንግር ዞን፣ በጎደሬ ወረዳ በጉማሬና በካቦ ቀበሌዎች የሚገኝ 5000 ሄክታር በደን የተሸፈነ መሬት በኢንቨስትመንት ስም እንዲሸጥ መወሰኑን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ አሰምተው ነበር። በወቅቱ ውሳኔውን “በባዕድ ወራሪ ሃይል እንኳን የማይፈጸም” በማለት የተቹና ቅሬታቸውን የገለጹ ነበሩ።