በዳዊት ሰለሞን
የፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ ባልደረባ መሆኔ ጋዜጣዋን ማተሚያ ድርጅቱ አላትምም ያለበትን ምክንያት ከሶስተኛ ሰው እንዳልሰማ አድርጎኛል፡፡ስማቸውን እንዳንጠቅስባቸው የተማጸኑ አንድ ሃላፊ‹‹ሰዎች እየደወሉ ይህ ጋዜጣ ባለስልጣናቱን የሚሳደብ በመሆኑ ማተም የለባችሁም››ብለውናል ስለዚህ አናትምም በማለት ነግረውን ነበር፡፡የሰደብነው፣ያዋረድነው ባለስልጣን የትኛው ነው;ይህንንስ ያደረግነው በየትኛው ህትመት ነው;ሰውዬው ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ሳይፈቅዱ ተለዩን፡፡ አሁን አንድ ወዳጄ በፌስ ቡክ ገጹ ለዚህ ተቃራኒ የሆነ የብርሃንና ሰላም ደምበኛን ይዞ ቀርቧል፡፡በምስሉ ላይ የምትመለከቱት ጋዜጣ ስያሜ ህዳሴ ሲሆን ባለቤቷ ገዢው ፓርቲ ነው፡፡የጋዜጣው የጀርባ ገጽ አንድ ሰው ሲሸለም ያሳያል (ልክ እንደ ሚሊኒየር ገበሬዎችን ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሸልሙ እንደነበሩት) ፡፡ሸላሚው የኢህአዴግ ጉባኤ በሚመስለው ፓርላማ ተቃዋሚዎችን በመወከል አንድ መቀመጫ ያገኙት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ናቸው፡፡በግርማ የሚሸለመው ሰው ላይ‹‹ህገ መንግስቱን መጣስ››የሚል ጹሁፍ ተለጥፏል፡፡የጋዜጣው የካርቶን ስዕል መልእክት ድብቅ አይደለም፡፡ግርማና የግርማ የሆነ ሁሉ ህገ መንግስቱን የሚጥስ ነው በማለት ሽብር መፍጠር ነው፡፡አንድ የምክር ቤት አባልን እንዲህ መወንጀል ለብርሃንና ሰላም ወይም ለእነ አቶ ሽመልስ ከማል ወንጀል ያልሆነበት ምክንያት አይገባኝም፡፡
በነገራችን ላይ ፓርላማው የአባላቶቼ መልካም ስም ጎደፈ በማለት ለአዲስ ጉዳይ መጽሄት ማስጠንቀቂያ ጽ ፏል፡፡እንዴት ነው ነገሩ አቶ ግርማ የምክር ቤቱ አባል አይደሉምን ; በአደባባይ ማስረጃ በሌለበት ሁኔታ ህገ መንግስቱን መጣስን ይሸልማሉ በማለት ሲወነጅላቸው ምነው የአዲስ ጉዳይ ከሳሾች ህዳሴን ዘነጓት;
ብርሃንና ሰላም ድርጅት ኢህአዴግ ሲመታ ማልቀስ ካልዳዳው በስተቀር ደምበኞቹን በእኩል አይን መመልከት ግዴታውና ሃላፊነቱ ነው፡፡አልያ ፍኖተ ነጻነት መንግስትን ስትተች ተሳደበች እያለ መዝጋት የህዳሴን የተገለጠ ስድብ ደግሞ እንደ ምርቃት በመቁጠር ልዩነት ማድረግ ስውሩ እጅ ጋር ከማድረስ ውጪ ምንም ትርጉም አይኖረውም፡፡እርግጥ ነው የዚህ መድሃኒቱ የራስን ማተሚያ ማሽን መግዛትና ያን ግዜ ደግሞ የሚሆነውን ማየት ነው፡፡ ይብላኝለት ለብርሃንና ሰላም እንጂ እኛማ በተባበረ ርብርብ ማሽኑን ልንገዛው ነው፡፡
ተዛማጅ ፅሁፎች:
No comments:
Post a Comment