የኃይል እርምጃ ለህዝብ መልስ አይሆንም!
የትግላችንን ሂደት ለመግታት መንግስት ከውስጥም ከውጪም የተለያዩ ጥቃቶችን ሲሰነዝር መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በጥቃቱ ሙስሊሞችን ከትግሉ ሜዳ ለማስወገድ ታስቦ የነበረ ቢሆንም መንግስት የሚያስበውን ያህል ሲሳካለት ግን አልታየም፡፡ ይህ የመንግስት ጥቃት ሌት ተቀን አከብረዋለሁ ቢሎ በሚለፍፍለት፣ በተግባር ግን ሊገዛለት የማይፈቅደውን ሕገ መንግስት በመጣስ በተደጋጋሚ የተፈጸመ ነው፡፡
በሌላ በኩል የመንግስት ባለስልጣናት ባለፈው ሳምንት ተጠርቶ የነበረውን ሰላማዊ ሰልፍ አስታከው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጲያዊያን ሙስሊሞች ከአንድ ዓመት በፊት ያነሱትን ሃማኖታዊ ጥያቄ ለህዝብ ያላቸውን ንቀት በሚያሳይ ሁኔታ ድብቅ አጀንዳ ያለው አድርገው ለመሳል ሞክረዋል፡፡ በነገው የተቃውሞ ትእይንታችን እነዚህን ሁለት አንኳር ሐሳቦች 18 ወራት ቆይተው ምላሽ ከተነፈጓቸው ጥያቄዎቻችን ጋር በማስተሳሰር ድምጻችንን በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች እናሰማለን፡
በቀዳሚነት በደሴ ከተማ ሙስሊሞች ላይ በቅርቡ የተወሰደውን የኃይል እርምጃ በስልጠና፣ በማስፈራራትና በመደለል አልሳካ ያለውን መንግስታዊ እስልምና (አህባሽን) በመስጂዶቻችን የማንገስ፣ ሙስሊሙን ከመስጂዱ የማፈናቀል ሴራና በግልፅ በአፈሙዝ በመታጀብ መስጂድ ድረስ መግባቱ የመንግስት ለሕግ አልገዛ ባይነት ምን ያህል እንደደረሰ ያሳያል፡፡ ይህን የተጋረጠብንን አደጋ መላው ህዝብ ይበልጥ እንዲረዳው ማድረጉ ይበልጥ ትግላችንን እንደሚያጠነክረው በማመን በደሴ የተወሰደውን እርምጃ በነገው ተቃውሟችን እናወግዛለን፡፡
ባለፈው ሳምንት የተካሄደውን ሰላማዊ ሰልፍ ተንተርሶ መንግስት በሰላማዊ የትግል እንቅሴያችን ላይ ያካሄደውን ዳግመኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደምናወግዝና ትግላችንን ‹‹የፅንፈኞች›› እና ‹‹የአክራሪዎች›› በሚል መፈረጅ፣ የትግላችንን ሃገራዊነትና ህዝባዊነት በአደባባይ መካድና ህዝብንም በጅምላ ፅንፈኛ ማለት ወንጀል መሆኑን በተቃውሟችን እናሳስባለን፡፡
* ከማንም ከምንም በላይ የተላቀው ፈጣሪያችን አላህ መሆኑን ለሦስት ደቂቃ ‹‹አላሁ አክበር!›› በማለት እናውጃለን!
*ግንቦት 16 በደሴ ከተማ ሸዋበር መስጂድና ከዚያም ቀደም በተለያየ ጊዜ የመንግስት ሃይሎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ እየወሰዱት ያለው የሃይል እርምጃ ብርታትን ቢጨምርልን እንጂ እንቅስቃሴያችንን ፈጽሞ እንደማያቆመው ለሦስት ደቂቃ ‹‹በሃይል… አንረታም!›› በማለት እናረጋግጣለን!
* መንግስት በተለያየ ጊዜ በእንቅስቃሴያችን ላይ የሚነዛቸው አሉባልታዎችና የሃሰት ክሶች እንቅስቃሴያችንን በፍጹም እንደማያደናቅፉትና የከሸፉ ፕሮፖጋንዳዎች መሆናቸውን ለማሳየት ለሶስት ደቂቃ ‹‹የሃሰት ክስ…. አይገዛንም!›› በማለት እናረጋግጣለን!
* ሙስሊሙ ህብረተረሰብ ያቀረባቸው ሶስት መሰረታዊ ጥያቄዎች አሁንም ድረስ መልስ ያልተሰጣቸው በመሆኑና ተቃውሞውም መልስ ሳይገኝ የማይቆም መሆኑን ለመግለጽ ለሦስት ደቂቃ ‹‹ጥያቄው… ይመለስ!›› በማለት እናሳስባለን!
* መሪዎቻችንን ጨምሮ በመላ አገሪቱ ወህኒ ቤት ያለ ምንም ወንጀላቸው ሙስሊም በመሆናቸው ብቻ በእስር የሚገኙ ዓሊሞችና ዳዒዎች እንዲፈቱ ለሦስት ደቂቃ ‹‹እስረኞች…. ይፈቱ!›› እንላለን!
በመጨረሻም ሁላችንም ባለንበት ለሦስት ደቂቃ አላህ የመጣብንን ፈተና እንዲያነሳልንና እስረኞቻችን እንዲፈታልን ዱዓ በማድረግ የዕለቱ ተቃውሞ በአላህ ፈቃድ ይጠናቀቃል፡፡
አላሁ አክበር!
No comments:
Post a Comment