Tuesday, 16 October 2012

የወያኔ የዕድገት መለኪያ ምንነት

ማንኛውም የመልካም አስተዳደር ሥርዓት ያስፈነና ውጤት ከራሱ ጀምሮ በአካልና በአዕምሮ የፀዳ መሪ ያላቸው ሃገሮች ስለሁለንተናዊ እድገታቸው ሲያስቡ ቀዳሚው ተግባራቸው የሚያደርጉት የዜጎቻቸው የዴሞክራሲያዊ መብቶች ሙሉ በሙሉ መስፈናቸውን ቀጥሎም በተግባር ተተርጉመው መከበራቸውን ተከታታይነት ባለው ቁጥጥርና ክትትል ማረጋገጥ ነው።


ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የሚናፍቁትን ሃገራዊ ልማትና ዕድገት በዜጎች ሙሉ ተሣትፎ ማረጋገጥ ይሆናል። ከዚህ እውነታ ባፈነገጠ ኢ-ዲሞክራሲያዊ አካሄድ እየተጎዙ መጠቀማቸው ለመንግሥት በሆኑ የመገናኛ ዘርፎች በውሸት የታጀለ መግለጫና ፕሮፖጋንዳ በማናፈስ እየመራሁህ ነው በሚሉት ህዝብ ላይ መቀለድና ማላገጥ ለትዝብት ደርሆ እንደሚያስተውለው ኃይል የሆነውን ፍቅሩንና አመሄታውን ከማጣት የዘለለ ትርፍ አያስገኝም። የግለሰብ መብት ባልተከበረበትና ነፍጥ ባነገቱ የፌዴራል ፖሊስ እና ልዩ መቼ የመከላከያ ሠራዊት ቡድኖች ከየቤቱ እየተጎተተ በጥይት አረር ተጠብሶ በሚሞትባት ሃገር ስለዴሞክራሲ የሚያወራ በእብለት የሰባ ልሣን ምን ያህል ያልተገራና አሣፋሪ መሆኑን የሚያሳይ ሃቅ ነው።

ለዚህም በማስረጃነት በቅርቡ በአፋር አካባቢ የተፈፀመው ግፍ አረጋጋጭ ነው።.... ጉዳዩ እንዲህ ነው ነፍጥ በትከሻው፣ የፀጉር ሚዶ (ማበጠሪያ) በጎፈሬው፣ ረዘም ያለ መፋቂያ በጥርሱ መያዝ ነባር ባህላዊ እሴቱ የሆነውን የአፋር ብሔረሰብ አካል የሆነ ወጣት ጠመንጃህን ካልነጠቅንህ በሚል ትንቅንቅ ህይወቱ በፌዴራል ፖሊስ አባላት ትጠፋላች...በቀጣይ የአንድ ፌዴራል ፖሊስ ከነባለቤቱ መገደልን ከች ቤተሰብ ጋር በማያያዝ ቤተሰቦቹን በጥይት መደብደብ ምን ያህል ያለው ሥራት ፋሺስታዊ ባህርይ እንዳለው ማረጋገጫ ነው።


ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚገርመው ሌሎች በመንግሥት ማረሚያ ቤት የነበሩ ሁለት አፋሮችን አውጥቶ በጥይት መደብደብ አስቃቂነቱ ግልጽ ነው። የወያኔ መንግሥት እየፈፀመ ያለውን ይህን መሰሉን ግፍ ለህዝብ ያጋለጡ ጋዜጠኞችንና በተቃዋሚ ፖርቲ አባልነት ንቁ ተቃዋሚ የሆኑ ስላማዊ ዜጎችን ``አሸባሪ`` የሚል የውንጀላ ታፔላ በመለጠፍ የሃገሪቱን ማረሚያ ቤቶች የዜጎች ስቃይ መስፈሪያ ሲኦል ማድረጉ ዴሞክራት ነኝ ለሚለው የወያኔ መንግሥት የዴሞክራሲ መገለጫ ከሆነ የሥርዓቱ መስራችና ቀዳሚ ተቀባይ የሆኑት አውሮፓውያኑ እንዴት ዘነጉት የሚያስብል ጉዳይ ነው።

በፋኖስ ብርሃን ቢታሰስ በህዝብ ታአማኒነትን ያፈራ የመንግሥት መዋቅርና ሹም ከማይገኝባቸው ሃገሮች መካከል በቀዳሚነት ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ስለመሆንዋ የሚያግት አይደለም። የወያኔ መንግሥት የዝግ ስብሰባው አጀንዳ በሥልጣን ላይ እድሜን ስለማራዘም መሆኑን ተፈጥሮአዊ መብቱን ተነፍጎ በዝምታ የተለጎመው ህዝብ የሚያውቀው ሃቅ ነው።

ሕዝብን በጎሳና በጎጥ ከፋፍሎ ከዚህ በፊትም ሆነ ራሱንም በተለያዩ የሃገሪቱ ክልሎች እርስ በእርስ እንዳላፋጨ ሁሉ ዛሬም የንፁሃን ደም ማፍሰስና ሲፈስ ማየት የእርኩስ መንፈሱ ሱስ ማርኪያ የሆነው ዘንድ በሃይማኖት ልዩነት የሚፈጠርን አደጋ ለመጋበዝ ለዘመናት ተከባብሮ በኖር ሕዝብ መካከል የመገለጫና ውንጀላ ክብሪት እየጫረ ይገኛል።

ወያኔ ድርጅታዊ ጡንቻውን ለማፈርጠም በልማት ስም በተቀረፀ አንድ ርዕስ (የአባይ ግድብ) ዜጎችን በመ/ቤታቸው፣ በልጆቻቸው ት/ቤት፣ በዕድሮች፣ በመኖሪያ አካባቢ በገንዘብ አዋጡ ጥያቄ እንደ እሳት በሚያቃጥል የንሮ ውድነት የተጠበሰውን ሕዝብ እያዋከበ ይገኛል።

እጀ-እርዥሙ ሕወሃት ለዛሬ ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ለቀጣዩ ዘመናትም የሚያደባ በመሆኑ በገለልተኛነቱ ፊቱንም ታአማኒነት የሌለውን የምርጫ ቦርድ ሎሌዎቹ ሣይለወጡ ሕዝቡን በነፃ የመምረጥ መብትን ጠልፎ የሚጥልበት ወደሮ እየተበተበ ይገኛል። ለሥልጣኑ ሙት የሆነው ይሄው አምባገነን መንግሥት ይህን የሚከውነው ርሃብን ለመተንተን በዓለም አቀፍ ደረጃ ማጣቀሻ የሆነችውን ሃገራችንን በሌላ የውርደት ማጣቀሻ ለማሣወቅ ፍትሃዊ ባልሆነውና በጎሣ አመለካከት ከታወረ ህሊናው በሚመነጩ ሕዝቡን ለርሃብ፣ ለፍትህ እጦት በዳረጉት ፖሊሲዎቹ በማማረር ስደተኛነትን ብሔራዊ መታወቂያችን እያደረገ ይገኛል።

ለዚህም በኮንቴነር ውስጥ ታሽገው በመሰደድ ላይ ሣሉ በአየር እጦት ህይወታቸውን በማጣርት አስከሬናቸው ለሃገራቸው አፈር ሣይታደል በባዕዳን ሃገሮች ተቀብርው የቀሩ ዜጎቻችን በቂ ማረጋገጫ ናቸው።

መልካም አስተዳደር ያለው መንግሥት ኖሮት በምግብ እራሱን ችሎ በልቶ ሲያድርባት ሃሳቡን በነፃነት በመግለፅ ከህሊና ርሃብተኝነት የታደገ መሆን ሲችል ብቻ እንጂ ከወያኔ መንግስት ጋር በሥርዓቱ ¨ልማታዊ ነጋዴ¨ የተሰኘ የቁልምጫ መጠሪያ በተቸራቸው ጥቂት ሕወሃት ወለድ ነጋዴዎችና በረሃ ወለድ የወያኔ ጄኔራሎች(በወረቀት ላይ የ3ሺ ብር ደሞዘተኞች) በየቦታው በተቆለሉ ህንፃዎች በዘመነኛው የቅኝ አገዛዝ ወረራ ከተካኑ የውጭ ሃገር መንግሥታትና ዜጎች .... ብድር ለአበዳሪው ቀላል.... ለከፋዩ እዳ እንዲሉ የህዝቡ የዘመናት እግረ-ሙቅ በሆነው የብድር ገንዘብ የተነጠፉ መንገዶች በቀን አንዴም እንን ለመብላት ለተሳነው አያሌ ዜጋ ተቆርሶ የሚበላ ዳቦ ወይም ተጠቅልሎ የሚዋጥ ፓስታ አይደለም።

እናም በሃገሪቱ ምስኪን ሕዝብ በርሃብ ተገርፎ በየቀኑ ከህይወት ወደ ህልፈት እየተሸጋገረ ባለበት ወቅት የሃገሪቱ ዕድገት መለኪያ ተደርጎ ጫካም ሣለ ይሄን ያህል ገደልኩ በማለት በቁጥር ድርደራ በማይታማው የወያኔ መንግሥት የፕርሰንት ማጣፈጫ ከመሆን ባለፈ በዚህ በሰለጠነ ዘመን በርሃብ እየተገረፈ እና በከተማው ያሉ የቆሻሻ ገንዳዎችን ለርሃብ ማስታገሻ የሚበላ ባገኝ ብሎ በመቆፈር ብዙሃኑ ዜጋ እየሞተ ሣለ ህንፃዎቹንና መንገዶቹን ማን እንዲገለገልባቸው ነው? ምላሽ የሚሻ ጥያቄ ቢሆንም የሚሰማ ጆሮ ያለው መንግሥት ለማግኘት ስላልታደልን ምላሽ የለውም።

ምክንያቱም ዛሬ በሃገሪቱ ውስጥ ርሃብ የሌለው ቤተ መንግሥት ውስጥ ብቻ ነውና ነው። ወያኔ ዛሬ አለ ለሚለው ዕድገት ማሣያ የሚጠቅሰው የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ታስቦ ሣይሆን ከጋራ ህንፃዎች ጀርባ ያለው ሴራ በአንድ አካባቢ ለረዥም ጊዜ በአብሮነት የኖረው ህዝብ ለተቃውሞም ሆነ ለአመፅ አንድ ልብ ሆኖ ሊነሳብኝ ይችላል በሚል ስጋት እየባነነ ያለውን ይህንኑ የወያኔ መንግሥት ሕዝቡን በተለያዩ አካባቢዎች በመበታተን የእፎይታ የአየር ስዓት ለማግኘት ስለመሆኑ የብዙዎች እምነት ነው።

ይህ ፍትሃዊ የዕጣ ድልድል የሌለው የጋራ ቤቶች ማስተላለፊያ ሂደት ኢ-ፍትሃዊነቱ የሚጀመረው ከቀበሌ አስተዳደር ጀምሮ ነው። ይሄውም ተቃዋሚ ናቸው ተብሎ ለእጣ አውጪው አካል ቀድሞ ስማቸው ከተላከ በኃላ ከእጣ ዝርዝሩ ውስጥ እንዳይካተቱ ይደረጋል የሚለው ከእነሱ ጉያ የወጣ የማንነታቸው ማረጋገጫ ደባ ነው።

ለዚህም በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ያለውን ብዙሃኑን ዜጋ ይሄው የቤት እጣ በጨረፍታ እንን አለማየቱን ለማረጋገጥ እሩቅ መዝ አያስፈልግም። ይሄውም በሃገሪቱ ዋና መዲና ውስጥ ዕድሜአቸው ከ10 እስከ 15 ዓመት የሚደርስ ሴት ህፃናት በምሽት ቁር ከዋና መንገዶች ዳር ቆመው በውርጭ እየተጠበሱ በድህነት አራንቋ ውስጥ ያሉ ቤተሰቦቻቸውን እህል ለማቃመሰ “አልጋ ፈላጊ” በማለት የሚንገላቱበትና መጠለያ አልባ ዜጋውም ከጎዳና አዳር ላይ ይሻላል በማለት ገላውን ለተባይ ገብሮ ሌሊቱን በእንቅልፍ ላይ ሣይሆን በስቃይ የሚያሣልፍበት የዕለት ተዕለት የሰቆቃ ትዕይንት ድምር ካልሆነ በስተቀር ወያሄ ኢህአዴግ ከ11-12…በመቶ ዕድገት እያለ የሚያንቋርረው የዕብለት ቀመር የእውነትነቱ መሠረት እውሸትና እውሸት ብቻ ነው።

ኢትዮጵያ በአውሮፓዉያን አቆጣጠር እስከ 2015 ከቻይና ከሕንድ ቀጥሎ በእኮኖሚ እድገቷ ከዓለም ሦስተኛ ትሆናለች በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከድህነት ተላቃ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች አንዷ ትሆናለች እያሉ የዋሆችን በጨረቃ የተጋገረ ዳቦ እየመገቧቸው እንደሆነ ከሰማን ሰነባበትን።

እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ለመሆኑ የችግሩ ሰለባ የሆነውና ኑሮውን እየኖረ ያለው ሕዝባችን በሚገባ ያውቀዋል።ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ሊመጣ የሚችለው የግብርናው ክፍል እድገቱን ጠብቆ ሲሄድና የኢንዱስትሪው ክፍል ከፍተኛ እድገትን ፈጥሮ ከሰማንያ በመቶ የሚሆነው ሕዝባችን ለሚተዳደርበት የግብርና ክፍል የሥራ ዕድል ሲፈጥር እንዲሁም የሠራተኛው የኑሮው ሁኔታ ሲለወጥና ዕድገታችንም በሕብርተስባችን የኑሮ ሁኔታ ማየት ስንጀምር ብቻ ነው።

የአገራችን ተጨባጭ እውንታው ግን 2011 በወጣው የተባበሩት መንግስታት የሕዝብ ዕድገት መለኪያ ሪፖርት እንደሚያሳየው አገራችን ከ187 አገሮች መካከል 174ኛ በመሆን በድህነት በሁሉም ረገድ ወደ መጨረሻ ካሉት አገሮች ትመደባለች። የአብዛኛው ሕዝባችን በቀን ገቢው ከ1. 25 ዶላር በታች መሆኑ በከፍተኛ ድህነት አርንቆ ውስጥ ለመሆናችን ሌላ ዋቢ እንድንጠራ አይገፋፋንም።

በሴቶች እህቶቻችን ላይ የደረሰው ሰቆቃ በየአርብ አገራቱ እራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለማሸነፍ ሲሉ አገር ለቀው የተሰደዱ፤  በሄዱበት የአረብ አገራት የሚደርስላቸው አጥተው የድርሱልኝ ጥሪ ለኢትዮጵያ ኢንባሲ ተብየው ሲያቀርቡ ጆሮ ዳባ ልበስ ይባላሉ፤ ይህንን ያየ ባሃድ በነብሳቸው ሲጫወት ተመልካች አቶ እንደውጣ የቀረው ስንቱ ነው። መቼ በአረብ አገራት ያበቃል የኢትዮጵያውያን ስደት ፍትህና ነጻነት አገኝ ብሎ ጥገኝነት ለመጠየቅ ወደ ተለያየ አገር ሲጓዝ ውሃ የበላው መንገድ የቀረው ስንቱ ኢትዮጵያዊ  ነው። ለዘመናት የሚውራለት እድገት መጨርሻው ስደት ነው ውይስ  ይህ እድገት ከቤተመንግስት ወጪ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያን ሳየመለከታቸው ቀርቶ ነው? ኢኮኖሚያችን አድል እያሉ ሲያደነቁሩን ከወሬና ከፖለቲካ ድራማ ያልዘለለ ለስልጣን እድሜ ማራዘሚያና ለአወሮፓውያን ታአማኒነትና ተቀባይነት ለማግኘት ሲል ያልሆነውን ሆነ ያልተሰራውን ተሰራ በማለት ከአንድ መሪ ተብዪ የማይጠበቅ የሐሰት ንግግሮችን ለዘመናት አዳመጥን።

ኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ የለቅሶ ስርዓት በማሳሰቢያና በትዛዝ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ለቅሶ እንዲደርስ በቀበሌ ድንኾን ተተክሎ በግዳጅ እንዲያለቅስ ሙሾ እንዲያወርድ እንዲሁም ጋዜጠኞች ስለሚመጡ ጥቁር ለብሳቹ ኑ በማለት ይህን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሰገዳጅ ሁኔታ ያለማቆረጥ ለ15 ቀናት ሲጉላላ እንደነበር የተመለከትነው ነው።

መቼም ይህ ሁሉ ጎንበስ ቀና መሪያችን ዲሞክራሲያዊ አመራር ነበሩ፣ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነትና ተውዳጅነት ነበራችው የሚል አንድምታ ያለው ሲሆን፣ ያለተደረገውን ያልሆነውን ነው ብሎ ለታይታ የተቀነባበር ዝግጅት እንደነበር ለመረዳት አስረጂ አያስፈልገውም። እውነታውና የብዙሃኑ የሃገራችን ሕዝብ ኑሮ ግን ከላይ በትንሿ ለመጠቃቅስ እንድሞከርኩት ነው።

ለመሆኑ ወያኔ ለሥልጣን ከበቃበት ጀምሮ በዚህ በዘረኛው መሪ ትዕዛዝ የስንቱ ቤት ባዶውን ቅርቷል! ሀገራችንን የባህር በር ያሳጣን፣ የዘር ማጽዳት ወንጀል በአርሲ፣ በጋምቤላ፣ በኦጋዴን ያስፈጸመ!!

የእምነት ተቋማትን የደፈረ የሃይማኖት አባቶችንና ምዕመናን ያሰረ የገደለ! (በአንዋር መስጅድ አዎሊያ ትምህርት ቤት በአርሲ እንዲሁም በጎንደር ኢየሱስ አደባባይ የተፈጸሙት ያስተዉሉ) ሠርቶአደሩን ጸጥ ለጥ አርጎ ለመብቱ እንዳይናገር ተናግሮ ከተገኛም ከሥራው በማስወገድ እሱንና ቤተሰቡን በረሃብ በመቅጣት የታወቀ! አርሶ አደሩን ከቀየው በማፈናቀል መሬቱን ለባዕዳን በመቸብቸብ በአገሩ ስድተኛ ያረገ!

መምህሩ የመብት ጥያቄ በመጠየቁ ብቻ ሥራውን ያሳጣው! ጋዜጠኞች ፈራ ተባ እያሉ ትንሽ ትንሽ እንኳ በብዕር እንምክራቸው በማለታቸው በሽብርተኝነት አስፈርጆአቸው በእስር የሚያማቅቃቸው! (ሪኦት አለሙንና እስክንድር ነጋን ያስተውሉ) ለሕዝብና ለአገር ብሩህ ተስፋ ያላቸውን ዜጎችን ሁሉ ወያኔዎች ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ ደብዛቸውን በማጥፋት በመግደል የሰባዊ መብት ተሟጋቹንና የህግ ባለሙያ (አቶ ተስፈዬ ታደሰን ያስተውሉ) እቤቱ ደጅ እንደ በግ ያሳረዱ!
  
ሕዝባዊ አመኔታና ፍቅር ያላቸውን ሕብረ ብሄር ድርጅቶችን በአገራቸው ፖለቲካ ሂደት ተሳታፊ እንዳይሆኑ በተራ ሴራ ማገድ (ኢሕአፓን ያስተውሉ) መሪዎቻቸውን በማሠር በማፈን ደብዛቸውን ማጥፋት (እነ ጸጋዬ ደብተራውንና አበራሽ በርታን ያስተውሉ) በምርጫ 97 ደግሞ የ14 ዓመት ዕድሜ ሕጻናትን በአልሞ ተኳሽ ነፈሰገዳዮች ያስፈጀ!

ሕዝቡ ድምጼን አክብሩልኝ በማለቱ ብቻ ወጣቱንና ጎልማሳውን ቦዘኔ በማለት ከ40-50ሺ ዜጎች በየወታደራዊ ማሰልጠኛ በማጎር በደርቅ ምላጭ በማስላጨት በአንድ ምላጭ ብዙ ሰው እንዲላጭ በማርግ ለተላላፊ በሽታ የዳረጋቸው የአውሬ መጫዎቻ ያረጋቸው ይህ ሟቹ የወያኔ ቁንጮ ነው። በእውነቱ የነዚህ ሁሉ ቤተሰቦችና ወዳጆች ሁሉ ለገዳያቸውና አስገዳያቸው ደረት ደለቁ ማለቱ ትልቅ መሳታት ነው። ይህ ሁሉ ግፍና መከራ እንኳን አሁን በትኩሱ ቀርቶ የወደፊት ትውልድ የማይረሳው ክፉና መጥፎ የሆነው የወያኔ ታሪክ ተመዝግቦ ይቀመጣል። የገዢና የግዳጅ ለቅሶ ከቶ ይህን የቆሸሸ የሟቹን ስዕብናና የእናት ድርጅቱን ታሪክ አይቀይረውም አይለውጠውም!!
በመጨረሻም በወያኔ ሥርዐት በሕዝባችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ግፍና ጭቆና ለተወሰነ ጊዜ ይቀጥል ይሆናል ግን ግን እመቃና በደል በታሪክ ህላዊ ሆኖ አይታወቅም ሕዝባችንም በቆራጥ በልተቋረጠ መራራ ትግሉ ከዚህ አስከፊ አገዛዝ ራሱን  ነጻ  እንድሚያወጣ ቅንጣት ያህል አንጠራጠርም።

እናም የወቅቱም የአገራችን ሁኔታ ለዚህ የተመቻቸ ይመስላልና ቆራጥ ድርጅቶች በታሪካቸውና በዓላማቸው የጸኑ  የጎደፈ ታሪክ የሌላቸው የአገራችንና የሕዝባችንን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው ያልሰጡ ከወያኔም ሆነ ከምዕራቡ ዓለም በየጓሮው የማይሞዳሞዱ ይህን ምቹ ሁኔታ ተጠቅመው በአገራችንና በሕዝባችን መሃል በመሆን ጥገናዊ ሳይሆን መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ትግሉን በግንባር ቀደምትነት ይመሩታል ብለን እንጠብቃለን።

 
ከማርታ ሕብስቱ


ነፃነት ለኢትዮጵያ ሕዝብ

ኢትዮጵያ እጆቾን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች

ቸር ይግጠመን



No comments:

Post a Comment