Wednesday, 3 October 2012

``ላም ባልዋለበት......``

 ከማርታ ህብስቱ
ኖርዌይ

በሴቶች መብት ላይ የሚደርሱ ተፅህኖዎችንና የጾታ ጥቃቶችን በተመለከተ በመላው ዓለም ላይ ያልተደረጉ ጥናቶችና ያልተፈተሹ ድርሳኖች የሉም። ለዚሁ የህብረተሰቡ አካል የሆኑ ወገኖች ቁልፍ ችግር መፍትሄ ለመስጠት ብዙ ሃገሮች የትግሉ ድርሻ ለባለጉዳዮቹ ሳይባሉና ሳይተው የየሃገሪቱ ዜጎች አጋርነታቸውን አሳይተውበታል።

ብዙዎችም ለይስሙላ ያህል ሳይሆን በሴት እህቶቻችን መብትና እኩልነት ላይ ጫና ከሚፈጥሩ ኋላ ቀር ባህሎችና ልማዶች ጉያ ስር የተፈለፈሉ ያልተጻፉና የተጻፉ ህጎች ውስጥ የአፈናው መሳሪያ የሆኑ ህጎችን በማረም ለዕድገታቸው የላቀ አስተዋጽኦ ሰጪ ከሆነ የድል ምዕራፍ ላይ እንዲደርሱ አስችሎቸዋል። በሃገራችን በኢትዮጵያ ውስጥ ወንድና ሴት የተለያየ አመለካከት እንዳይኖራቸው ጋሬጣ በሆነ ሥርዓት ውስጥ እንዲያድጉ በሆነበት ሁኔታ የግንዛቤ ለወጥ ለማምጣት ብዙ ማውራት ሣይሆን የተወራለትን በጎ ነገር ወደ ተግባር ማሸጋገሩ ወሳኝ ቢሆንም ቅሉ ትኩረት የተቸረው ባለመሆኑና ዓለም አቀፍ የትኩረት አቅጣጫን ለማስቀየር ብቻ ማደራጀት ከሚል ሽፋን የራቀ አይደለም።በሃገራችን ውስጥ ሴቶች በማህበር በዕድር መደራጀት የጀመሩበት ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም ያፍሩላቸው ፋይዳ የለም። ማናቸውም አደረጃጀት በገዥው በኩል የገደብ አጥር የታጠረለት ነውና ያንን ሾልኮ ለማለፍ የመናገርና የመፃፍ መብት በታፈነባት ሃገር የሚታሰብ አይደለም ምክንያቱም ሴቶች ተደራጀተውበታል የሚባለው አደረጃጅት ያለባቸውን የመብት ረገጣና የጾታ ጥቃት ለማስወገድ የሚታገሉበት መሣሪያ ሣይሆን የገዥውን የፖለቲካ ድርጅት የጭቆና ዜማ እንዲያቀነቅኑ በመመሪያ የተጠፈሩበት የአፈና አገዛዝ ሥልት ነው።

ይህም ለመሆኑ በንጉሡ ዘመን የነበሩ የሴቶች የበጎ አድራጎት፣ የደርግን አብዮታዊ የሴቶች ማህበር (አኢሴማ) እና የኢህአዲግ ሥርዓትን የሴቶች ማህበር ሚናና ተልዕኮ በትውስታ መቃኝት በቂ ነው። ስለ ወያኔ ከጀምሩ ኢ-ዲሞክራሲያዊ ስለመሆኑ አንዳንድ ድርጊቶችን ጠቆም አድርጊ ማለፍ እወዳለሁ፤ ወያኔ አሸንፌ ገባሁ ካለበት ዘመን ጀምሮ በሴቶች ላይ ያደረሰውን ጭቆና ከጅምሩ ማስታወስ እወዳለሁ። 

ለምሳሌ ያህል አበራሽ በርታ ወያኔ አፍኖ ደብዛዋን ያጠፋት እህታችን ትሙት ትኑር ባልታወቀ
ሁኔታ ላይ እያለ፤ እንዲሁም ብርቱካን ሚደቅሳን ንግግርሽ አላማረኝም በሚል ፈሊጥ ብቻ በሥር እንድትሰቃይ ካደረገ በኋላ ሃገር ለቃ እንድትሰደድ አድርጎአታል። አሁን ደግሞ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙን በሽብርተኝነት ወንጅሎ ለእሥር በመዳረግ ትንናት ፋሽስታዊ ደርግን በመፋለም አይኗን እስከማጣት የደረሰችውን አበራሽን ደብዛዋን በማጥፋት፣ በዛሬዋ ብዕርተኛ በርዕዮት ላይ በፈጸማቸው ድርጊቶች ብቻ ወያኔ ምንያህል ጸረ ዲሞክራሲና ጸረ ህዝብ ለመሆኑ ተያያዥነት ያላቸው የወያኔን ከውልደቱ እስከ እድገቱ ያሉ የባህርዉ መገለጫዎቹ ናቸው።

ስለዚህም ሴቶች በህብረተሰቡ ቀጣይ የፖለቲካ፣ የኤኮኖሚና የማህበራዊ ዕድሎች ላይ ተስፋ እንዲኖራቸው የሚያስችል ዕድል ያልፈጠረ ነው። በስመ ዴሞክራሲ በማስመሰል ለማንሆለል ሲባል ” የሴቶች መብትና የጾታ ጎዳይ ትኩረት ተሰጥቶት በብሔራዊ አጀንዳ ውስጥ ተካተተ” ከምን ባለው የፕሮፓጋንዳ ድለላ ባሻገር በቀጣይነት የሚፈነጥቀው ብሩዕ ተስፋ የለም። ለዚህም በዋቢነት ለመጥቀስ ያህል የስብአዊ መብት ጥሰት መላው ዓለምን ባስገረመና መነጋገሪያ እድትሆን በገዥዊች
በተገደደች ሃገራችን ውስጥ ሴቶች ከሚያደርስባቸው የመብት ረገጣና የጾታ ጥቃት የመዳን ተስፋ ይኖራል ብሎ መገመት አይቻልም። ብዙዎች ሚሊየነር ሆኑ ተብሎ ከሚነገርላቸው የሃገሪቱ ገጠራማ ክፍል ጎጆአቸውን ዘግተው ወደ ከተማ በመፍለስ ለሴተኛ አዳሪነት እና ለጎዳና ተዳዳሪነት ተዳርገው የሚጎሳቀሉ ወገኖችን ማየት የሃገሪቱ የዕለት-ተዕለት ተከታታይ ትርኢት ሆኖል። ከዚሁ በተጨማሪም በግዳጅ እየተደፈሩ ካሉ ሴቶች የሚውለዱ ህፃናት በካርቶንና በእራፊ በየጎዳናውና በየስርቻው የሚጣሉባት፣ የሚያሳድጉበት አቅም በማጣት ልጆቻቸውን ለህገ-ውጥ የጉዲፈቻ ገበያ የሚቀርብባት አሳዛኝ ሃገር ሆናለች። ይህን መሰሉ ዘግናኝ ተዕይንት እንደ ልማት እስካልታየ ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ የሴቶችና የህፃናት ጉስቁልና ከላቀ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያረጋግጥ ነው። የሃገራችን ሴቶች ዘርፈ ብዙ በሆኑ የጥቃት ሰለባዎች መካከል ያሉ ናቸው። 

በባልና ሚስት መካከል በተፈጠረ አለመገባባት በአካል ጥቃት የተጎዳች እህት ዳኝነት ፍለጋ ወደ ህግ-አስፈፃሚ ተብዬ አካላት ደጅ ስትርግጥ የምትሸኝው ደግሞ ህሊናዋን በሚያደማ ምላሽ ነው። ``በባልና ሚስት ጉዳይ አያገባንም`` የሚል ይሄ ደግሞ ብዙዎቹ ዜጋ መሆናቸውን ከመጠራጠር አልፎ
ተፈጥሮአቸውን እስከመርገምና መጥላት ያደረሰ ነው። ይህ ደግሞ የሚያሳየው ያለው ሥርዓት ለሴቶች መብት አለመከበርና ለጻታ ጥቃት መወገድ ቀርቶ ለመከላከሉ እንኳን ምንም ፍላጎትና ዝግጁነት እንደሌለው የሚያሣይ እውነት ነው። ሴቶች የህብረተሰቡ ግማሽ አካል እንደመሆናቸው መጠን በማናቸውም ሃገራዊ ጉዳዮች ያላቸው የግል አመለካከት መመዘኛ ሣይሆነ የዜግነት መብታቸው በዝምታ ወይም በይፋ ባልተነገረ አዋጅ ያጡ ናቸው። የሴቶች ተሣታፊነት አለ የሚሉ ወገኖች የታላላቅ ባለሥልጣን ሚስቶች አሊያም ለገዢው የፖለቲካ ድርጅት ያላቸው ታማኝነትና ወገናዊነት ግምገማ በሚሉት ማጣሪያ ተጣርቶ ያለፉትን ብቻ ካልሆነ ብዙሃን የሃገሪቱን ሴቶች ነው ቢባል ከተለመደው ቅጥፈት የዘለለ አይደለም። በግምገማ ማጣሪያ ተጣርተው የታዩትም ቢሆን ከታች የቀበሌ አስተዳደር ጀምሮ እስከ ቀጣዩ የሥልጣን እርከን ሥር ሆነው በጾታ መብት አለመከበርና ጥቃት ሥር ያሉ ሴቶችን በየቀበሌው እየሰበሰቡ የፖለቲካ እምነታችንን ተቀበሉ በማለት የሥርዓቱን ጭቆና መብት ነው ብለው በመቀበል አሜን እንዲሉ ጫና ፈጣሪ ከመሆን ባሻገር በሴትነታቸው ያለውን ጭቆና የሚታገሉበት መድረክ የላቸውም ተልዕኮአቸውም ለዚህ አብይ ጉዳይ ስላልሆነ አይታሰብም በሌላው መልኩ ደግሞ በተወካዮች ምክር ቤትም ተብየው ቢሆን ጾታዊ ተሣትፎ አለ ለማስባል ብቻ የተወከሉ የማጨብጨብና በልማታዊ እንቅስቃሴ ውስጥም ቢሆን በባሬላ ድንጋይና
አሸዋ ለመሸከም በየመንገዱ ዳር ሽንኩርትና ቃሪያ ለመቸርቸር እንኳን የሥርዓቱ ቀንደኛ አጋፋሪዎችን አወዳሽና አጃቢ መሆን እንደ ቅድመ ሁኔታ በተቀመጠባት ሃገር ከጽሑፍ የዘለለ ተግባር ማየት የማይታለም ከሆነ ከራርሞል። በኢትዮጵያ ውስጥ ጥቂት የተማሩ ሴቶችም ቢሆኑ በታላላቅ የመንግሥት መ/ቤቶች ጭምር ባላቸው ሙያዊ ብቃት የሚመዘኑ ሣይሆን እንደ ፋሲካ በግ ሴትነታቸውን ለባለሥልጣናት ፍላጎት ማርኪያ እንዲያቀርቡ ያልተፃፈ ግዴታ አለባቸው። ይህንን ጾታዊ ጥቃት ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ እህቶች ባላሰቡትና ባልጠበቁት የፖለቲካ ውንጀላ ተፈብርኮ እንደ ታፔላ ተለጥፎባቸው ወደ ወህኒ እንዲወረወሩ ይደረጋል። አብዛኛዎቹም ቀጣዩን ጥቃት በመስጋት ሃገር ጥለው ለስደት ይዳረጋሉ። ለዘመናዊ ባርነት ተዳርገው የሚደርስባቸው ግፍና በደል ከመዘርዘር የሰሞኑን በሊቢያ ምድር በአንድት እህታችን ላይ ተፈጽሞ ያየነው ነገር ከብዙ ሺሆች ውስጥ አንዷን ሸዋየ ሞላን ብቻ ነው።

ከዚህም ውጭ በሃገሪቱ አብዛኛው ባለሥልጣን ሥልጣንን በሥልጣን ላይ ተደርቦ በስተቀር ብዙሃን ሴቶችን ለሥልጣን ማብቃት ከዲስኩር አልፎ የተተገበረ አይደለም። መናገር ወንጀል ሆኖ ልጅዋ ታስሮባት የምትንጎጠጠው ወይም አቅርቢ በሚል ዛቻ መቅኖ አጥታ የሰቀቀን ህይውት የምትገፋው ቁጥር እየናረ ያለባት ሃገር ሆናለች። ባጠቃላይ የሴቶች መብትና የጾታ እኩልነት መብት ከዜጎች የስባአዊ መብት መከበር ተለይቶ ሊመጣና ሊገኝ የማይችል ነው። ስለዚህም የስባዊ መብቶችን በተለያዩ የሽፋን ስሞች በተለበጡ አፋኝ መዋቅሮች ተተብትቦ በተረገጠባት ሃገር ውስጥ የሴቶችን የመብትና የጾታ እኩልነት መናፈቅ ``ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ`` እንደሚባለው የሃገር ቤት አባባል ጉምን መጨበጥ ነው። ስለሆነም እኛ ከሃገር ውጭም ሆነ በሃገር ውስጥ ያለን ሴቶች የጾታ ድላችንን ለመጎናፅፍ ዋንኛ የሆነው የዜጎች ስብአዊ መብት እንዲከበር የጋራ የሆነ ድምፃችንን ማሰማት ወቅቱ የሚጠይቀን የዜግነት ግዴታ ነውና እናብር። ለዚሁም እኛ በውጪ የምንገኝ ሴቶች በዓለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች ድርጅታ(ዓኢሴድ) ማዕቀፍ ሥር ተደራጅቶ መታገል የግዜው ወቅታዊ ጥያቄ ነው። በህብረት ድምጻችንን ለማሰማት በድረጀት መታቀፈ አማራጫችን አድረገን ተሳትፎአችን እንደቀጠልን ነው። ከምስረታው ጀምሮ የኢህአፓ እንቅስቃሴ ግማሽ ክፍል የሆኑት ሴቶች እስከ አሁን ለድርጀቱ የእንቅስቃሴ ታሪክ ይህ ነው የማይባል ድርሻ ማበረከታቸውን ሳንረሳ.....
ኢሕአፖ የሴቶች ጥያቄ ተገቢውን ሚዛን ሰጥቶ ትግል ሲያካሂድ ወጣት ሴቶች የጥናት ክበብ ዙሪያ
ተደራጅተው ለጥቆም የራሳቸውን ማህበር እንዲያቆቁሙ በማበረታታት ነበር የተጀመረው። በየካቲት
አብዮት ጊዜም የሴቶች አስተባባሪ ኮሚቴን በመመስረት የሴቶችን የመብት ትግል ለማጠናከር የአቅሙን ጥሮዓል። ኢሕአፖ የሴቶች ትግል በወንዶች ሞግዚትነት የሚካሄድ ነው ብሎም ስልማያምን ሴቶችን በመቀስቀስና በአጠቃላዩ ትግል በማስለፍ የነቁትና የተደራጁት ሴቶች እህቶቻችውንና እናቶቻቸውን የማደራጀትና የማታገሉን ግዳጅ በቅድሚያ እንዲሸከሙ አድርጎል። ኢሕአፖ የሴቶችን ድርብ ጭቆና ማወቁ የመጀመሪያው እርምጃ ነበር። ኢሕአፖ የሴቶች በጾታቸው እየደረሰባቸው ያለውን በደል ቦታ ባለመስጠት ሁሉም ነው የሚበደለው በሚል ሽፋን የሴቶችን የመብት ጥያቄ ወድ ጎን የሚያደርጉ ብዙ ናቸው። ሴቶች በራሳቸው የመደራጀታችውን መብትና አስፈላጊነቱም ኢሕአፖ ቢቀበልም ሌሎች ደግሞ ሴቶች በአጠቃዩ በሚታገል ድርጅት ውስጥ መኖራቸው ይበቃስ በሚል የወንዶችን----ተራማጅነን ባዮቹን ጨምር- ትምክህት ሸፋፍነው ያልፉታል። በሀገራችን ቀርቶ በባዕድም ቢሆን ሴቶች ከነፃነት ደማቸውን አፍሰው የተባለው ሀገራዊ ነፃነት ሲገኝ ግን ሴቶች ከጭቆና ወደ ጭቆና ከመሸጋገር ሌላ መብታቸውን አለማግኚታቸውን አይተናል። ኢሕአፖ የተቀበለውን እስከተወሰነ ደረጃም ተግባራዊ መሆኑን ያረጋገጠው ሌላ አቢይ ጉዳይ የሴቶች ድርጅት አንፃራዊ ነፃነት እንዲኖረው ያሻል የሚለውን መርህ ነው። አኢሴማ ወይም ወያኔ የሚቆጣጠረው የሴቶች ማህበር ዓይነት ሳይሆን ነፃ የሆነና ሴቶችን የሚወክል ሴቶች የሚቆጣጠሩት የሴቶች ድርጅት መኖሩ ወሳኝ ነው። ውንዶች ወይም አገዛዙ የሚቆጥጠሩት የሴቶች ድርጅት በመሰረቱ የወንዶች ድርጅት ወይም መሳሪያ ነው።

ምንጭ፦ ማን ያውራ የነበረ ነሐሴ 26\1998 ኢሕአፖ የታወጀበት
34 ኛ ዓመት መታሰቢያ

No comments:

Post a Comment