Saturday, 12 January 2013

አገር አቀፍ የዚያራ ሳምንት ፕሮግራም እስከ ረቡዕ ድረስ ቀጥሎ ይውላል!


ድምፃችን ይሰማ

አላህ ይርዳን! አላህ ይቀበለን! አሚንበአላህ ስም እጅግ በጣም ሩሕሩሕ እጅግ በጣም አዛኝ
አገር አቀፍ የዚያራ ሳምንት ፕሮግራም እስከ ረቡዕ ድረስ ቀጥሎ ይውላል!
ቅዳሜና እሁድን እጥፍ ድርብ ምንዳ ባለው ስራ እንጠቀምበት፡፡

አገር አቀፍ የዚያራ ሳምንት ፕሮግራም እስከ ረቡዕ ድረስ ቀጥሎ ይውላል!
“365 ቀናት ለሀይማኖት ነፃነት” መርሃ ግብር ሁለተኛ ሳምንት መጀመሩን አስመልከቶ ሳምንቱ በአገር አቀፍ ደረጃ በዚያራ ደምቆ እንደሚውል ማወጃችን ይታወሳል፡፡ ይህን ተከትሎ አላህ ብሎ በድል ማግስት ትውልድ የራሱን ታሪክ በሚያነብበት ጊዜ የታሪክ ጣፋጭ አካል ሆኖ ሊመዘገብ የሚችል በርካታ አስደማሚ መረጃዎች እየደረሱን ይገኛሉ፡፡ ህብረተሰባችን በትክክልም የሚያኮራ ታሪክ እየሰራና የማይፋቅ አሻራም እያሳረፈ ይገኛል፡፡

የዚያራ ታሪካችን በኢትዮጵያ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው፡፡ ለኛ ለሙስሊሞች ግን ትርጉሙ ከዚህም የላቀ ነው፡፡ የመብት ጥያቄዎቻችንን ለመንግስት አቅርበው ምላሽ ይዘው እንዲመጡ ብለን በአስር ጣታችን ፈርመን የወከልናቸውን መሪዎቻችንን የፊርማችን ቀለም ሳይደርቅ ወሕኒ ሲወረውሩብን በአንድ በኩል የተሰለፍንለትን ዓላማ ሳናዛንፍ በገባነው ቃል ኪዳን መሠረት ትግላችንን በመቀጠል በሌላ በኩል ደግሞ ለታሳሪ ወኪሎቻችን ያለንን ክብር፣ ፍቅር፣ አለኝታና ምስክርነት ለማረጋገጥ በሰው ጎርፍ ቃሊቲን በማጥለቅለቅ ሕዝብ ታሪክ ሰራ-አልሐምዱሊላህ፡፡ የኮሚቴዎቻችንን እምባ አበስን፣የደረሰባቸውን መከራና ስቃይ ላፍታም ቢሆን እንዲረሱት አደረግን፣ ልቦናቸው በሀሴት ፈነደቀች፡፡

ዛሬ በዚህ ሳምንት ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ታሪክ እንሰራለን፡፡ የታሳሪ ኮሚቴዎቻችን ቤቶች ካመት በፊት እንደማንኛውም ቤት አባወራ አባወራ ይሸቱ ነበረ፣ ዛሬ ግን ጭር ብለዋል፣ ልጆቻቸው ያባቶቻቸውን ገላ ካሸተቱ ከራረሙ፣ በናፍቆት ተቃጥለዋል- ማን እንዳባት! ቤተሰቦች ደጅ ደጅ ማየት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ ግን ደግሞ በዚህ ሳምንት በልዩ ፕሮግራም ይህንን ሁሉ ለማስረሳት እነሱን በመዘየር አለንላችሁ እንላለን፣ እነሱን ያጣችኋቸው እናንተ ብቻ ሳትሆኑ እኛም ነን በማለት ቤታቸውን ቤታችን እናደርጋለን- በልዩ የዚያራ ስርዓት…. በአዲስ አበባ የቃሊቲን ማረሚያ ቤት ጨምሮ በሌሎች ያገራችን ክልሎች እስር ቤት ለዚያራ የተጓዙት እግሮቻችንን ዛሬ ወደ ቤተሰቦቻቸው እናዞራቸዋለን…ይህ ፕሮግራም አገር አቀፍ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ከአላህ እጥፍ ድርብ ምንዳ ማግኘትን ታሳቢ በማድረግ ቅዳሜ እና እሁድን እንዲሁም ቀጣዮቹን ቀናት እንጠቀምባቸዋለን ኢንሻአላህ፡፡

ሌላ ዋና ነገርም አለን…መንግስት አረመኔያዊ እርምጃ ወስዶ ለዲናቸው ስለ ቆሙ ብቻ ወንድሞቻችንን ገድሎብናል፡፡ ነጥቆናል፡፡ እርግጥ ነው እነኚህ ሸሂዶቻችን ናቸው፡፡ አላህ ደግሞ ሙታን ናቸው አትበሉ፤ህያው ናቸው እንዲያውም በጌታቸው ዘንድ ይረዘቃሉ ይለናል፡፡ እነሱ አኼራ ሲሄዱ ቤተሰቦቻቸውን ደግሞ አላህ ይጠብቃቸዋል፤ሆኖም የኛ በሂወት መኖር ያለምክንያት አይደለም….ሰበብ ነን፡፡ቤተሰቦቻቸውን የመንከባከብ ሰበቡ በኛ ላይ የወደቀ ተግባር ነው፡፡ይህ የሁል ጊዜ ተግባራችን ቢሆንም በዚህ ሳምንት ግን በልዩ ፕሮግራም ያሉበትን ቦታ አነፍንፈን የቲሞቻችንን ፀጉር ማበስ ይኖርብናል፣ ቤተሰቦቻቸውን መዘየር ይኖርብናል- የሸሂድ ቤተሰቦችን እንዘይራለን፡፡ በተለይ ቅዳሜና እሁድ! 
ይህ ሰላማዊ ትግላችን የሁላችንንም ቤት በር አንኳኩቷል፡፡ መጠኑ ይለያይ እንጂ በአገር አቀፍ ደረጃ ሁሉም ሙስሊም የጉዳት ሰለባ ነው፡፡ ይሁንና ያንተ ይብስ ያንቺ ይብስ መባባል ከዲን ፍቅር ነውና… በትግላችን ሂደት ውስጥ የተደበደቡ፣ የቆሰሉ፣ታመው የተኙ…በጠቅላላ ቀላልም ሆነ የባሰና ከበድ ያለ ጉዳት የደረሰባቸውን ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም ቤተሰቦች ያሉበትን ቦታ አነፍንፈን፣ አድራሻ የምናውቅ ለማናውቅ እየተጠቋቆምን፣ እየተረዳዳን በዚህ ሳምንት እንዘይራለን-ኢንሻ አላህ፡፡ በተለይ ቅዳሜና እሁድን፡፡ 
ለዚህ የዚያራ ፕሮግራም ለየት ያለ ፕሮግራም ማዘጋጀት አያሻውም:: ጉዳዩን ሁሉም በባለቤትነት በመያዝና በመተጋገዝ ዚያራ የሚያስፈልጋቸውን በሙሉ አንዱን ከሌላው ሳናስበልጥ፣ ሳንለይ፣ ሳናስቀር በአላህ ፈቃድ በተቻለን መጠን እንዘይራለን፡፡

አላህ ይርዳን! አላህ ይቀበለን! አሚን

No comments:

Post a Comment