Saturday, 26 January 2013

የኢትዮጵያ ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔትና የጭቆናው መረብ!



መስፍን ግርማ ከኖርዌይ \ጃንዋሪ 2013\

ኢትዮጵያ ውስጥ የተዘረጋው አፈናና ጭቆና ከምን ጊዜውም በበለጠ አይነቱን እየቀያየረ የሰው ልጅ ፍትህ ነፃነት እየተነጠቀ ያለበት ሰዓት ነው።  የስልጣን ጥማት አራራው ያልወጣለት ወያኔና ግብረ አበሮቹ የምንለውን ብቻ ስሙ እንጂ አትጠይቁ፣ አትናገሩ፣ ለምን፣ እንዴት፣ ወዴት የሚለው ጥያቄ የማይስማማቸው የሰውን ደም እንደ ውሃ በማፍሰስ የሚረኩ አሁንም ይህ አመለካከት በሰፊው ጠንክሮ ተወ ባይ በማጣታቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬም የወያኔን ቀንበር ተሸክሞ ጀርባው ተልጧል።

በቅርቡ እንዃን እየተፈፀመ ያለው ይህ ነው የማይባል ግፍ ነው። ሰዎች ያለምክንያት የሚሰቃዩባት፣ የሚገደሉባት እንዲሁም ዜጎች እንደ ሁለተኛ ዜጋ የሚታዩባት አገር እንደሆነች ብዙ ማስረጃ እየወጣ ነው። ለምሳሌ ያህል  የውጭ ኢንቨስተር ተብዬዎች ኢትዮጵያውያን ዜጎች ላይ የሚያደርሱት ግፍና ጭካኔ ይህ ነው ተብሎ የሚያልቅ አይደለም። ስንቶች ናቸው የሥራ የደሞዝ እንዲሁም ጥቃቅን መብታቸውን ሲጠይቁ በአጸፋው የሚመለስላቸው ተስፋ አስቆራጭ መልስ እንደሆነና ዳግም የመብት ጥያቄ እንዳያነሱ ከከባድ ማስጠንቀቂያ ጋር የሚነገራቸው ከመኃላቸውም ጥቂት የማይባሉትን ወደ ሞት እና ከባድ ወደሆነው እስር ይወረወራሉ። ሌላው እጅግ የሚያስገርመው በሃይማኖት ጣልቃ እየገባ እኔ አውቅላችዋለሁ በማለት ለኦርቶዶክሱም ለሙስሊሙም የኃይማኖት ተከታዮች መሪዎችህን መምርጥ የምትችሉት እኔ ባዘጋጀሁት መድረክ ካልሆነ አሸባሪዎች ናቹሁ በማለት ማስፈራራቱ መዛቱ ማሰሩ አልበቃ ብሎት እንደገና በጦር መሳሪያና በዱላ ደብድቦ መግደል ማን አለብኝነት እንደሆነ ነው የምንረዳው። ገዥው ቡድን የፓርላማ አሻንጉሊቶችን ሰብስቦ እያሳሳቀ በኢትዮጵያ ህዝብና በሉአላዊነቷ ላይ ሲቀልድ እንደነበር የሚታውቅ ነው። ነገር ግን አሁንም ሌሎች መሰሎቹ መለስ በከተባቸው መሰረት ከወገን ይልቅ ስልጣን ከአገር ይልቅ ለባዕዳን የሚለው ጭፍን አመለካከታቸው በጅጉ ጎልቶ የሚታይበት ሁኔታ ነው እያየን ያለነው። የወያኔ ቡድን ዜጎችን በኃይማኖት በብሔርብሔረሰብ በፖለቲካና በመሳሰሉት ከፋፍሎ እርስ በርስ ለማጫረስ ለማለያየት እኩይ ምግባሩ በተወሰነ መልኩ ቢሰራለትም፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወደ አንድነት ስለተመለሰ ወያኔ እንደፈለገውና እንደጠበቀው የእርስ በእርስ መተላለቁ ሳይሳካለት ቀርቶአል። ይህንንም እንደ ምሳሌ ማስቀመጥ ይቻላል። አማረኛ ተናጋሪ ከቀየው ሲፈናቀል የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች ይህንን የወያኔን ድርጊት ተቃውመው የአቋም መግለጫቸውን እና የተለያየ የትግል ስልት የሆነው ድምጹን አሰምቶል። የሙስሊሙን ሕብረተሰብ  የመብት ጥያቄ የእኩልነት እንደመሆኑ መጠን ሊደገፍ ይገባል።  ወያኔ በሃይማኖት እጁን ጣልቃ ያስገባበት ዋናው ምክንያት የሃይማኖት ብጥብጥ በኢትዮጵያ እንዲነሳ ስለሚፈልግና በዚህ አጋጣሚ የራሱን የስልጣን ጊዜ ለማራዘም የተጠቀመበት እንደሆነ መገመት አያዳግትም።

ወያኔ በሕገ መንግስቱ እንዳሰፈረው መንግስት በኃይማኖት ጣልቃ አይገባም ብሎ እራሱ ወያኔ የጻፈውን ሕግ መልሶ ራሱ የሚሽረው እንደሆነ ይታወቃል። አንድም ቀን የጻፈውን ሕግ ያላከበረ በስራ ላይ ያላዋለ መንግስት እራሱ በሕግ የማያምን ሆኖ እየታወቀ፤ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች ጋዜጠኞች እንዲሁም ነፃ ዜጎች ያገሪቱ ሕገ መንግስት በሚፈቅደው መሠረት እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ሁኔታ ወያኔ የዜጎችን ነፃነት ለማፈን ሲል የአሸባሪ ሕግ ብሎ አንቀጽና ቁጥር ጠቅሶ ለማንገላታት እንዲመቸው አድማጭ እንጂ ተናጋሪ እንዳይኖር መብታቸውን ነፍጎ የወያኔን ጫና በዝምታና በፍርዓት አሜን ብለው እንዲቀበሉ ማደርግ የፖለቲካ ዝቅጠት ነው። በፍትህ ቤት ወይም በፍርድ ቤቶች ያለው ሁኔታ እንደሚታወቀው ለሕግ የቆሙ ሳይሆን የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ ወይም ካድሬዎች መሆናቸውን ያሳያል ።

በየትኛውም ቦታ በትግል ወስጥ ያሉ እና እንዲሁም በተለያየ ሁኔታ ለነፃነት የሚታገሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ካሉበት በመጠራራት ትግሉን ማጠናከር እና ለውጤት ማብቃት አለባቸው። ምክንያቱም ገበሬ ይሁን ወዛደረ አባቶችና እናቶች በየቦታው እንደ ዕቃ ተጥለዋል፣ የወደፊት አገር ተረካቢ የሚያፈሩ አባቶችና እናቶች የደሞዝ ጥያቄ በማንሳታቸው ብቻ በችሎታ ማነስ ተብሎ ከሥራቸው ተባረዋል፣ ተፍናቅለዋል፣ ታስረዋል፣ ጠፈተዋል። ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሚያስፍልጋቸው የሥርዓት ለውጥ እንጂ የሰው ለውጥ አይደለም። የሰው ለውጥ እንደምናየው የተጻፈለትን የሚያነብ እንጂ በራሱ ምንም አይነት አመራር ማስተላለፍ የሚያስችል ነጻነት እንደሌለው፣ ለዚህም ከተናገረው ውስጥ ጥቄቱን ላስታውሳቹ በእስር ላይ ያሉት ጋዜጠኞችን እንዲህ ሲሏቸው ተሰምተዋል፤ እንደማይፈቱና ``ሁለት ቆብ አጥልቆ ጋዜጠኛ መሆን እንደማይቻል`` ልክ እንደ ሟቹ  የወያኔ ጠቅላይ ሚኒስትር አይነት ድራማ ሲሰሩ እያየን ነው። ይህ ማለት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አካላቸው እንጂ አስተሳሰባቸው ወይም ሥራቸውን የሚያከናውኑት ከጀርባቸው ያሉት ያረጁት ሕወሓት እንደሆነ ግልጽ ነው።

ተቃዋሚ ድርጅቶች ዓላማቸውን እውን ለማድረግ መደራጀትና አንድ ልብ መካሪ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን ድላቸውን ዕውን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ሁል ጊዜ የገዥውን አንባገነንነት ወያኔን እያወራን ጊዜ ማጥፋት ይብቃን በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ጥቄት አገር ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ አንባገነኖች በቃችሁ ልንላችው ይገባል። መቼም አንድ የምናውቀው ሚስጥር አለ ወያኔ ፈሪ መሆኑን ለዚህም ማረጋገጫ ኢትዮጵያውያን የመብት፣ የነፃነት ጥያቄ ሲያነሱ በዜግነታቸው የተሰማቸውን በብዕራቸው ሲያሳዮ አሸባሪዎች የሚል ስያሜ እየተሰጣቸው፣ እራሱ የሚል በፈጠረው ስጋት ንፁሃን ዜጎችን እያንገላታ እንደሆነ ይታወቃል። በማን አለብኝነት እየወነጀለ ወደ እስር የጣላቸው ጥቄቶች አይደሉም። ምክንያቱም ምንም ዓይነት ትጥቅ ሳያደርጉ በአመለካከታቸው ብቻ ነፃነታቸውን የተረጋጋ እና የሕዝቦቾ የበላይነት የሰፈነባት አገር እንደሚያደርጎአት እርግጠኛ ሰለሆነ ብቻ ነው።

ወደወጣቱ ክፍል ስንመለስ በአገር ቤት የሚደረግበት  የአፈና ዘዴ አንድ ለአምስት በሚለው አካሄድ ፅረ ዲሞክራሲያዊ እና ፅረ ሰላም አካሄድ መሆኑን ወጣቱ በውል ተገንዝቧል። ወጣቱ ወደ ስደት በገፍ መሄዱ በየቦታው መበተኑ መንከራተቱ በየበረሃውና በባህር መቅረቱ የሚያመላክተው አሁንም እንደበፊቱ በ66 እንዲሁም በደርግ ግዜ እንደነበረው ወጣቱ ከዚህ መንግሥት ጋር ቅራኔ እንዳለው የሚያመለክት ነው።

አንድ ጥያቄ አለኝ ለመሆኑ አለ የሚባለው ሕገ መንግስት መቼ ነው በሥራ የሚተረጎመው? ይህንን ጥያቄ ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም፤ ሟቹ መለስ በስንት ቀናቸው ትዝ አሉኝ! ብዙ ጌዜ ምላሳቸው ላይ የተነቀሱ እስኪመስል ድረስ እየደጋገሙ ``ሕገ መንግስቱን ለመናድ`` የሚል አባባል የሚጠቀሙት የቱን ሕገ መንግስት እንደሆነ ስላልገባኝ ወይም ስላላመንኩበት አለዚያም በሕገ መንግስቱ መስረት የተሰሩ ሥራዎችን ስላላየሁ ነው። በተለይ ዜጎች ለማሰር ለመግረፍ ለማሰቃየት፣ ለማፈን የሚጠቀሙበት የክስ ፋብረካቸው እና የፍርድ ሂደቱ አስገራሚ እና አሳዛኝ ምንም እወነትነት የሌለው ስለሆነ ጭምር ነው።

ለዛሬው በዚህ ይብቃኝ በሌላ ጽሁፍ እስከምንገናኝ ቸር እንሰንብት!
የኢትዮጵያ ሕዝብ ያቸንፋል!

No comments:

Post a Comment