ጄኔቫ ስደተኞች በየመን
ከየመን መውጣት የተሳናቸው ስደተኞች ቁጥርና የሚገኙበት ሁኔታም እጅግ አሳሳቢ መሆኑን ዓለም ዓቀፉ የስደት ጉዳዮች ድርጅት በእንግሊዘኛው ምህፃር IOM አስታወቀ ። የድርጅቱ ቃል አቀባይ ጁምቤ ኦማሬ ጁምቤ ከጄኔቫ ስዊትዘርላንድ በሰጡት መግለጫ በጎርጎሮሳውያኑ 2010 ፣ 53 ሺህ የነበረው የመን የሚገኙ ስደተኞች ቁጥር ባለፈው አመት ከእጥፍ በላይ አድጎ 107 ሺህ ደርሷል ። ከነዚህም አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያውያን ሲሆኑ የሶማሊያና የኤርትራ ስደተኞችም ያመዝናሉ ። በተለይ ስደተኞቹ ወደ ሳውዲ አረቢያ ለመሻገር የሚመርጧት ሃራድ የተባለችው ከተማ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች መነኻሪያ ናት ። ገንዘብ የሌላቸውና መድሐኒትም የማያገኙት እነዚሁ ስደተኞች የሚያድሩት አውላላ ሜዳ ላይ መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል ። ከዚህ ሌላ በሰሜናዊው የሃራድ ከተማ የሚገኝ ሆስፒታል ማንነታቸው ባልታወቀ ስደተኞች አስከሬኖች የተሞላ መሆኑንንም አስታውቀዋል ። በህገ ወጥ መንገድ ሰዎችን ከአገር ወደ አገር ከሚያሻግሩ ሰዎችና ፣ ከአፋኞች አምልጠው ወደ ድርጅቱ ቢሮዎች የሚመጡ በራካታ ስደተኞች አካላቶቻቸው ጉዳት የደረሰባቸው እንደሆኑም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል ። ድርጅቱ ባጋጠመው የገንዘብ ችግር ምክንያት ሃዳር ውስጥ ለ 3ሺህ ስደተኞች ያቀርብ የነበረውን ምግብ አቅርቦት 3 መቶ ለሚሆኑ ሴቶች አዛውንትና ብቻቸውን ለሚኖሩ ወጣቶች ብቻ ነው የሚሰጠው ። በገንዘብ እጥረት ምክንያት ድርጅቱ ያካሂድ የነበረው በፈቃድ ወደ ሃገር የመመለስ መርሃ ግብርም ለማቋረጥ መገደዱን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል ።
No comments:
Post a Comment